ተመልሳችሁ መሄድ እንዳለባችሁ አትዘንጉ!
1 “እንዴት ደስ የሚል ውይይት ነው! ለዚህ ሰው ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ አለብኝ።” ለራሳችሁ እንዲህ ብላችሁ ከተናገራችሁ በኋላ ያነጋገራችሁት ሰው የሚኖረው የት እንደሆነ ጠፍቶባችሁ ያውቃል? እንዲህ ከሆነ ተመልሳችሁ ሰውዬውን እንደምታነጋግሩት እርግጠኛ መሆን የምትችሉበት ብቸኛው መንገድ ማስታወሻ መያዝ ነው።
2 ሁሉንም ነገር በማስታወሻ አስፍሩ:- ፍላጎት ካሳየው ሰው ጋር ያደረጋችሁት ውይይት ገና ከአእምሮአችሁ ሳይጠፋ ጥቂት ጊዜ ወስዳችሁ ስለ ሰውዬው አስፈላጊ የሆኑትን መረጃዎች በሙሉ በማስታወሻ ላይ አስፍሩ። የሰውዬውን ስምና ልዩ ምልክቱን ያዙ። አድራሻውንም ጻፉ እንጂ ለመገመት አትሞክሩ። የጻፋችሁት አድራሻ ትክክል መሆኑን አረጋግጡ። የተወያያችሁበትን ርዕሰ ጉዳይ፣ ያነበባችሁትን ጥቅስ እንዲሁም ያበረከታችሁለትን ጽሑፍ በማስታወሻችሁ አስፍሩ።
3 በሚቀጥለው ጉብኝት ወቅት የምትመልሱለትን አንድ ጥያቄ አንስታችሁ ከሆነ በማስታወሻችሁ ያዙት። ስለ ሰውዬው፣ ስለ ቤተሰቡ ወይም ስለ ሃይማኖቱ የተገነዘባችሁት ነገር አለ? ካለ በማስታወሻ ያዙት። በሚቀጥለው ጉብኝታችሁ ስትገናኙ ይህንን መጥቀሳችሁ ሰውዬውን ለመርዳት ያላችሁን ፍላጎት የሚያሳይ ይሆናል። በመጨረሻም የመጀመሪያውን ውይይት ያደረጋችሁበትንና ለመመለስ ቀጠሮ የያዛችሁበትን ቀንና ሰዓት በማስታወሻ ላይ ጨምራችሁ አስፍሩ። ትክክለኛ ማስታወሻ ከያዝክ ያደረጋችሁትን ውይይት በደንብ ማስታወስ ከመቻልህም በላይ እንደምትመለስ የገባኸውን ቃል የመርሳትህ አጋጣሚ ጠባብ ይሆናል።—1 ጢሞ. 1:12
4 የተሟላ ማስታወሻ ከያዛችሁ በኋላ እንደ መጽሐፍ መያዣ ቦርሳ፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ማመራመርና ሌሎች ጽሑፎች ከመሳሰሉት የአገልግሎት መሣሪያዎቻችሁ ጋር ካስቀመጣችሁት ስትፈልጉት ለማግኘት ይቀልላችኋል። ቤታቸው ያልተገኙትን ሰዎች ለመመዝገብ የምትጠቀሙበት ከቤት ወደ ቤት መመዝገቢያ ቅጽ ተመላልሶ መጠየቅ የምታደርጉላቸውን ሰዎች ከምትመዘግቡበት የተለየ ቢሆን የተሻለ ነው። እርግጥ ነው፣ ትክክለኛ ማስታወሻ ለመያዝ ጥረት ማድረግ ተገቢ ቢሆንም ዋናው ቁም ነገር ግን ተመልሳችሁ መሄዳችሁ ነው!
5 ስለ ግለሰቡ አስቡ:- አገልግሎት ለመውጣት ስትዘጋጁ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ የያዛችሁትን ማስታወሻ ከልሱ። ተመልሰህ ስለምታነጋግረው ስለ እያንዳንዱ ሰው አስብና ምን ዓይነት አቀራረብ ብትጠቀም የተሻለ እንደሚሆን ገምት። ግለሰቡን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ለመምራት ፍላጎቱን እንዴት ማሳደግ እንደምትችል አስብ። እንዲህ ያለ ዕቅድ ማውጣትህ በምሥራቹ አገልጋይነትህ የምታገኘውን ስኬት ከማሳደጉም በላይ ደስታህን ይጨምርልሃል።—ምሳሌ 21:5ሀ NW
6 ስለዚህ በሚቀጥለው ጊዜ ጥሩ የሚያወያይህ ሰው ስታገኝ በቀላሉ አስታውሰዋለሁ ብለህ አትደምድም። ከዚህ ይልቅ ማስታወሻ ያዝ፣ የጻፍከውን ከልስ፣ ከተለያያችሁ በኋላም ስለ ግለሰቡ አስብ፣ በመጨረሻም ተመልሰህ ሂድ!