አምላክን የሚያስከብር መልካም ጠባይ ይኑራችሁ
1 የትም እንኑር የት ጠባያችን፣ አለባበሳችንና አጋጌጣችን ስለራሳችንም ሆነ ስለምናመልከው አምላክ ምሥክርነት ይሰጣል። የብዙ ሰዎችን ትኩረት በሚስቡት የአምላክ ሕዝቦች በሚያደርጓቸው ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ በተለይ ይህ ሁኔታ በግልጽ ይታያል። አርአያነት ያለው ጠባይ ስናሳይ የይሖዋ ስም ይከበራል። (1 ጴጥ. 2:12) ይሁን እንጂ ለአፍታ እንኳ መጥፎ ጠባይ ብናሳይ ወይም የግዴለሽነት ድርጊት ብንፈጽም በአምላክ ስምና በሕዝቦቹ ላይ ነቀፋ ልናመጣ እንችላለን። (መክ. 9:18ለ) የምናሳየው ጠባይ ሌሎች ሰዎች ስለ ድርጅታችንና ስለምናመልከው አምላክ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዙ ሊያደርግ እንደሚችል ማሰብ ‘ማንኛውንም ነገር ለአምላክ ክብር ለማድረግ’ ጠንቃቆች እንድንሆን ሊያደርገን ይገባል።—1 ቆሮ. 10:31
2 አርአያነት ያለው ጠባይ:- አብዛኛውን ጊዜ ሌሎች ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ባላቸው ሥርዓታማነት፣ መልካም ጠባይና አካላዊ ንጽሕና በጣም ይደነቃሉ። አንድ የሆቴል አስተዳዳሪ በሆቴሉ አርፈው ስለነበሩ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ቤተሰቦች እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥቷል:- “እስከ አሁን ካየኋቸው ልጆች ሁሉ እንደ የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች ጥሩ አላየሁም! አለባበሳቸው ልክ እንደ ትልቅ ሰው ነው፤ ጨዋ፣ ሰው አክባሪና ሥርዓታማ ናቸው፤ ምንም ዓይነት ችግር አይፈጥሩም። ልጆቻችሁ ስለሚያሳዩት ጠባይ በእርግጥ ልትመሰገኑ ይገባል። ልጆቻችሁን በማስተናገዳችን በጣም ተደስተናል።” የሚያስተናግዱን ሰዎች በይሖዋ ሕዝቦች መካከል የሰፈነውን ፍቅርና መከባበር ስለሚመለከቱ ወደፊትም ቢሆን ተመሳሳይ አስተያየት እንደሚሰነዘር እርግጠኞች ነን።
3 የጨዋ አለባበስ:- የልዩና የወረዳም ሆነ የአውራጃ ስብሰባዎችን የምናደርገው የትም ይሁን የት ቦታው እንደ መንግሥት አዳራሽ መታየት ይገባዋል። የጨዋ አለባበስና አጋጌጥ ሊኖረን እንደሚገባ ግልጽ ነው። ወንድሞችና እህቶች በስብሰባው ላይም ሆነ ከፕሮግራሙ በኋላ የዓለምን መንፈስ ከሚያንጸባርቅና ከሌሎች ሰዎች በምንም የማንለይ የሚያደርጉንን ጨዋነት የጎደላቸው ወይም ቅጥ ያጡ ፋሽን ልብሶችን ከመልበስ መቆጠብ አለባቸው። እህቶች የቀሚሳቸው አሰፋፍም ሆነ ቁመት ጨዋነት የጎደለው እንዳይሆን መጠንቀቅ አለባቸው። (1 ጢሞ. 2:9, 10) ልጆች ጂንስ ወይም ለጨዋታ ጊዜ የሚለብሱትን ልብስ ለብሰው ወደ ስብሰባ መምጣት የለባቸውም። የአውራጃ ስብሰባውን ስንካፈል፣ በምናርፍበት ሆቴል፣ በምግብ ቤቶችም ሆነ ዕቃ በምንገበይበት ሱቅ ለማንም ማሰናከያ የማንሆን የአምላክ አገልጋዮች መሆናችንን ማሳየት ይገባናል።—2 ቆሮ. 6:3
4 በዚህ ዓመትም በሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የጥምቀት ሥነ ሥርዓት የሚከናወነው ቅዳሜ ጠዋት ይሆናል። የሚያዝያ 1, 1995 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 30 በጥምቀት ሥነ ሥርዓት ወቅት ማሳየት ስለሚገባን ጠባይ ይገልጻል። ሁላችንም “ለጥምቀት የሚገባውን አክብሮትና ክብደት መስጠት ይኖርብናል። ፈንጠዝያ የሚታይበት ጊዜ አይደለም። በአንጻሩም መኮሳተርና ፊት ማጥቆር አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜም አይደለም” በማለት ገልጿል። ከሁሉም በላይ ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች በጣም የሚያጣብቁ ወይም ስስ በመሆናቸው ሰውነትን የሚያሳዩ ወይም ውኃ ሲነካቸው ሰውነት ላይ የሚጣበቁ የባኞ ቤት ልብሶች ተስማሚ ሊሆኑ አይችሉም። በመሆኑም ሁላችንም ክርስቲያናዊ ጥምቀት ያለውን ክብደትና አስደሳችነት ማንጸባረቅ ይገባናል።
5 ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘በቅዱስ ኑሮና እግዚአብሔርን በመምሰል ምን ዓይነት ሰዎች መሆን’ እንዳለብን አሳስቦናል። (2 ጴጥ. 3:11) በጉባኤም ሆነ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የምንናገራቸውና የምናደርጋቸው ነገሮች ልበ ቅን የሆኑ ተመልካቾች ክብርና ውዳሴ የሚገባውን አምላክ እንዲያውቁና እንዲያመልኩ የሚረዳ እንዲሆን እንመኛለን።—1 ቆሮ. 14:24, 25
(ወደ ገጽ 3 ዞሯል )
አምላክን የሚያስከብር . . . (ከገጽ 1 የዞረ )