መልካም አድርጉ ምስጋናም ይሆንላችኋል!
1 “እንደ እነዚህ ሰዎች የተረጋጋ ሕዝብ አይቼ አላውቅም።” “ከእነርሱ ጋር መሆን አስደሳች ነው።” እነዚህ ባለፈው ዓመት ከተደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎች በኋላ ከውጭ ሆነው የሚታዘቡ ሰዎች ከሰነዘሯቸው ብዙ አዎንታዊ አስተያየቶች ጥቂቶቹ ናቸው። (ምሳሌ 27:2፤ 1 ቆሮ. 4:9) በዚያም ሆነ በዚህ የሚወደሰው ይሖዋ ነው። (ማቴ. 5:16) “የአምላክ ቃል አስተማሪዎች” የተሰኘው የዘንድሮው የአውራጃ ስብሰባ ደግሞ አምላክ ሊወደስ የሚችልበት ሌላ ጥሩ አጋጣሚ ነው።
2 በየዓመቱ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ሊኖረን ስለሚገባው ተገቢ ምግባር በደግነት ማሳሰቢያዎች ይሰጡናል። ይህ የሚደረገው ለምንድን ነው? የዓለም አስተሳሰብ፣ አለባበስ እና ባሕርይ ይበልጥ እየተበላሸ ሲሄድ እኛ የእነርሱን አመለካከት መኮረጅ ስለሌለብን ነው። መልካሙ ስማችን እንዲበላሽ አንፈልግም። (ኤፌ. 2:2፤ 4:17) ለምሳሌ ያህል ጠዋት 2:00 ላይ የመሰብሰቢያው ቦታ በሮች ሲከፈቱ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች “የተሻሉ” መቀመጫዎችን ለመያዝ ሲሯሯጡ፣ ሲጋፉና ሲገፈታተሩ ይታያሉ። በዚህ ምክንያት አንዳንዶች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
3 ሰፊ ስርጭት ያለው የአንድ ጋዜጣ አዘጋጅ ባለፈው ዓመት ከተደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎች አንዱን በሚመለከት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከምንም ነገር በላይ የራሳቸው የምሥክሮቹ ምግባር ትኩረት የሚስብ ነው። ያን ያህል ብዙ ቁጥር ያላቸው ግርማ ሞገስ የተላበሱ ሰዎች መመልከት ምን ያህል መንፈስን የሚያድስ ነው! የተለያየ ዘርና ጎሳ ያላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች የክት ልብሳቸውን ለብሰው በጸጥታ ወደ መሰብሰቢያው ቦታ ይጎርፋሉ። ባሕርያቸው እስከ ዛሬ ወደዚያ ቦታ ከመጡት ሌሎች ተሰብሳቢዎች ሁሉ በጣም የተለየ ነበር።” አዎን፣ ልከኛና የሚያስከብር አለባበሳችን ያስመሰግነናል። ልጆቻችንም ቢሆኑ ወደ ስብሰባ ሲመጡ ጂንስ ወይም ሲዝናኑ የሚለብሱትን ዓይነት ልብስ አይለብሱም። አለባበሳችንና አጋጌጣችን ወይም ምግባራችን የአድማጮችን ትኩረት ከስብሰባው መንፈስ እንዲሰርቅ ፈጽሞ አንፍቀድ።—ፊልጵ. 1:10፤ 1 ጢሞ. 2:9,10
4 የጥምቀት እጩዎች ሥነ ሥርዓቱ የተቻለውን ያህል ክብር የተላበሰ እንዲሆን ለማድረግ ይጥራሉ። በሚጠመቁበት ጊዜ ልከኛ ልብስ መልበሳቸው ለዚህ የተቀደሰ ዝግጅት ያላቸውን አክብሮት ያሳያል። አስጠኚዎች ከስብሰባው በፊት ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻቸው ጋር በሚያዝያ 1, 1995 መጠበቂያ ግንብ እትም ላይ የወጣውን “የአንባብያን ጥያቄዎች” ቢከልሱ በጣም ጠቃሚ ይሆናል።
5 ሥርዓታማነታችንና አምላክን የሚያስከብር ጠባያችን ስለ ክርስቲያናዊ እምነቶቻችን የሚመሠክሩ ከመሆናቸውም በላይ ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ ያስችሏቸዋል። እንግዲያው ‘መልካም ማድረጋችንን እንቀጥል።’ “የአምላክ ቃል አስተማሪዎች” በተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ስንገኝ ምስጋና ይሆንልን ዘንድ ምኞታችን ነው።—ሮሜ 13:3