የጥያቄ ሣጥን
◼ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መጸለይ ያለበት ማን ነው?
በጉባኤ የሚቀርበው ጸሎት የአምልኮታችን ዋነኛ ክፍል ነው። ሌሎችን ወክሎ ወደ ይሖዋ መቅረብ የላቀ መብትና ከባድ ኃላፊነት ነው። ከዚህ አንፃር ሽማግሌዎች በስብሰባዎች ማን ጸሎት ማቅረብ እንዳለበት ሲወስኑ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ መጠቀም ያስፈልጋቸዋል። ጉባኤውን ወክለው ጸሎት የሚያቀርቡ የተጠመቁ ወንድሞች በጥሩ ምሳሌነታቸው የሚታወቁና የጉባኤውን አክብሮት ያተረፉ የጎለመሱ ክርስቲያን አገልጋዮች መሆን አለባቸው። አምላካዊ ፍርሃትና አክብሮት በተሞላበት መንገድ የሚያቀርቡት ጸሎት ከይሖዋ አምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዳላቸው የሚያሳይ መሆን አለበት። “ትሑት ልብ ይዞ በሌሎች ፊት መጸለይ” በሚል ርዕስ የወጣው የግንቦት 15, 1986 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) በተለይ ጉባኤውን ወክለው በሕዝብ ፊት ጸሎት ለሚያቀርቡ ወንዶች ጠቃሚ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዘረዝራል።
ሽማግሌዎች በአጠያያቂ አኗኗሩ ወይም ቁም ነገረኛነት የሌለው በመሆኑ የሚታወቅን ወንድም ጸሎት እንዲያቀርብ ማድረግ የለባቸውም። አንድ ወንድም ቁጣ የሚቀናው ወይም በሕዝብ ፊት የሚያቀርበውን ጸሎት የግል አለመግባባቶችን ለመግለጽ እንደ መሣሪያ አድርጎ የመጠቀም ዝንባሌ ያለው ከሆነ በሌሎች ፊት የመጸለይ መብት አይሰጠውም። (1 ጢሞ. 2:8) አንድ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ወንድም ቢጠመቅም ሽማግሌዎች ጉባኤውን ወክሎ ለመጸለይ የሚያስችል መንፈሳዊ ጉልምስና ይኑረው ወይም አይኑረው ማመዛዘን ይኖርባቸዋል።—ሥራ 16:1, 2
አልፎ አልፎ በአገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ላይ ቡድኑን ወክሎ ለመጸለይ ብቃት ያለው ወንድም በማይኖርበት ጊዜ አንዲት የተጠመቀች እህት ጸሎት ማቅረብ ያስፈልጋት ይሆናል። ሆኖም ስትጸልይ በተገቢ ሁኔታ ራሷን መሸፈን ይኖርባታል። የአገልግሎት ስምሪት በሚደረግባቸው ስብሰባዎች ላይ አንዳንድ ጊዜ ብቁ የሆነ ወንድም የማይገኝ ከሆነ ሽማግሌዎች ብቁ የሆነች እህት ስብሰባውን እንድትመራ መመደብ ይኖርባቸዋል።
የሕዝብ ስብሰባውን በሊቀ መንበርነት የሚመራው ወንድም የመክፈቻውን ጸሎት ማቅረቡ የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ በሌሎች የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ብቃት ያላቸው ብዙ ወንድሞች ካሉ ስብሰባውን ከሚከፍተው ወይም የመጨረሻውን ክፍል እንዲያቀርብ ከተመደበው ወንድም ውጭ ሌላ ወንድም የመክፈቻውን ወይም የመዝጊያውን ጸሎት እንዲያቀርብ ሊጠየቅ ይችላል። በማናቸውም ሁኔታ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ጸሎት እንዲያቀርብ የሚጠየቀው ወንድም የሚጠቅሳቸውን ነገሮች ማሰብ ይችል ዘንድ አስቀድሞ ሊነገረው ይገባል። እንዲህ ከሆነ ወንድም ለዚያ ስብሰባ የሚስማማ የተሳካና ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ይችላል።
እንዲህ ያሉት ጸሎቶች ረዥም መሆን አያስፈልጋቸውም። አንድ ወንድም በሕዝብ ፊት በሚጸልይበት ጊዜ ቢቆም፣ ሊሰማ የሚችል በቂ የድምፅ መጠን ቢኖረውና ግልጽ በሆነ መንገድ ቢናገር ብዙውን ጊዜ ሌሎች የሚለውን በሚገባ ሊረዱት ይችላሉ። ይህም የተሰበሰቡት ሁሉ ጸሎቱን እንዲሰሙና በመጨረሻም ከልብ በመነጨ ስሜት “አሜን” እንዲሉ ያስችላቸዋል።—1 ዜና 16:36፤ 1 ቆሮ. 14:16