ቀላል አቀራረብ ከሁሉ የተሻለ ነው
1 ወጣት አስፋፊዎች ብዙውን ጊዜ የመንግሥቱን መልእክት የሚያካፍሏቸውን ሰዎች ትኩረት የሚስቡት ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት አነጋገራቸው ቀላል ስለሆነ ነው። አንዳንድ አስፋፊዎች ውጤታማ ምሥክርነት ለመስጠት የረቀቀ አቀራረብ ያስፈልጋል ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ በተሞክሮ እንደታየው ቀላልና ግልጽ አቀራረብ ከሁሉ የተሻለ ነው።
2 ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት ያወጀው ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱም እንዲሁ እንዲያደርጉ አሰልጥኗቸዋል። (ማቴ. 4:17፤ 10:5-7፤ ሉቃስ 10:1, 9) የአድማጮቹን ትኩረት ለማግኘትና ልባቸውን ለመንካት ሲል ያልተወሳሰቡ መግቢያዎችን፣ ጥያቄዎችን እንዲሁም ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። (ዮሐ. 4:7-14) እኛም ምሳሌውን በመኮረጅ ሌሎች በቀላሉ የሚረዱትን አቀራረብ መጠቀማችን የተገባ ይሆናል።
3 የምናውጀው መልእክት “የመንግሥት ወንጌል” ነው። (ማቴ. 24:14) የአምላክን መንግሥት የንግግራችሁ ዋነኛ ርዕስ ማድረጋችሁ አቀራረባችሁን ቀላል ለማድረግ ይረዳችኋል። አድማጮቻችሁን ስለሚያሳስባቸው ነገሮች ተናገሩ። አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ይልቅ የቤተሰባቸው ጉዳይ ያሳስባቸዋል። አንድን አባት ይበልጥ የሚያሳስበው ዋናው ጉዳይ ሥራውና የቤተሰቡ ደህንነት ነው። ወጣቶች የወደፊቱ ሕይወታቸው፤ አረጋውያን ደግሞ ጤንነታቸውና ደህንነታቸው ያሳስባቸዋል። ሰዎች ብዙውን ጊዜ በሌሎች አገሮች ከተከሰቱት ነገሮች ይልቅ በአገራቸው የተከናወኑ ነገሮች ያሳስቧቸዋል። በጋራ በሚመለከቷችሁ ጉዳዮች ላይ ከተነጋገራችሁ በኋላ ትኩረታቸውን ታዛዥ የሰው ዘሮች በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር በሚያገኙት በረከት ላይ እንዲያደርጉ እርዷቸው። የአድማጮችህን ፍላጎት ለመቀስቀስ ቀላልና ታስቦባቸው የተመረጡ ጥቂት ቃላት ተናግሮ ይህንን በጥቅስ መደገፍ በቂ ነው።
4 እንዲህ በማለት ውይይት መጀመር ትችል ይሆናል:-
◼ “የሰው ዘር መድኃኒት ባልተገኘላቸው ብዙ በሽታዎች እየተሠቃየ ነው ቢባል እንደሚስማሙ እርግጠኛ ነኝ። አምላክ በቅርቡ ሁሉንም ዓይነት በሽታዎችና ሞትን ለማስወገድ ቃል መግባቱን ያውቃሉ?” መልስ እንዲሰጥ ከፈቀድክለት በኋላ ራእይ 21:3, 4ን አንብብ።
5 ግልጽና ቀላል አቀራረቦችን ተጠቅማችሁ በአገልግሎት ክልላችሁ ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች ስለ ይሖዋና ስለ ዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲያውቁ በመርዳት አእምሮና ልብ መንካት እንድትችሉ ምኞታችን ነው።—ዮሐ. 17:3