“አቋሜን ጠብቄ እጸናለሁ! እጸናለሁ! እጸናለሁ!”
1 ከጀርመኑ ታላቅ እልቂት በሕይወት የተረፈ አንድ ታማኝ ክርስቲያን የተናገራቸው እነዚህ ቃላት ናዚ የጭካኔ ተግባር ቢፈጽምባቸውም በእምነታቸው የጸኑትን በሕይወት ያሉትንም ሆነ የሞቱትን በሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ቁርጠኛ አቋም ያስተጋባሉ። (ኤፌ. 6:11, 13) ስላሳዩት ድፍረትና ስለተቀዳጁት ድል የሚገልጸው ልብ የሚነካ ታሪካቸው የይሖዋ ምሥክሮች የናዚን ጥቃት በጽናት ተቋቁመዋል በሚለው ቪዲዮ ውስጥ ተገልጿል። በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሁሉ ይህን ቪዲዮ አይተው ልባቸውን የነካቸው ምን እንደሆነና ምን እንደተሰማቸው ሐሳብ እንዲለዋወጡ ማበረታቻ ተሰጥቷል።
2 አእምሮአችሁን የሚያመራምሩ ጥያቄዎች እነሆ:- (1) የይሖዋ ምሥክሮች ናዚዎችን በመቃወም ድፍረት የተሞላበት አቋም የወሰዱባቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው? (2ሀ) ሰላምታ አሰጣጥን በተመለከተ ምን አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር? ለምንስ? (2ለ) ይህስ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቦችን የነካቸው እንዴት ነው? (3) በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ታስረው የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ስንት ናቸው? እዚያስ መለያቸው ምን ነበር? ከጌስታፖዎችስ ምን ይደርስባቸው ነበር? (4) ወንድሞቻችን ነፃነት ለማግኘት ሲሉ መለወጥ ያልፈለጉት ነገር ምንድን ነው? (5ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች የሂትለር መንግሥት ሲፈጽምባቸው የነበረውን ግፍ ለመቃወም ድምፃቸውን ያሰሙት እንዴትና መቼ ነው? (5ለ) የሂትለር ምላሽ ምን ነበር? (6) የይሖዋ ምሥክሮች እርስ በርስ መተባበራቸው ለእነሱም ሆነ ለሌሎች ሰዎች በመንፈሳዊና በሰብዓዊ ሁኔታ ሕይወት አድን ሆኖ የተገኘው እንዴት ነው? (7) በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የተደረሰው የመንግሥቱ መዝሙር የትኛው ነው? (8) የመጣው ቢመጣ ለይሖዋ ያለህን ፍጹም አቋም እንድትጠብቅ የሚረዳ ሆኖ ያገኘኸው ወንዶች፣ ሴቶችና ወጣቶች ያሳዩት የትኛው የታማኝነት ምሳሌ ነው? (በተጨማሪም የ1999 የዓመት መጽሐፍ ገጽ 144-7ን ተመልከት።) (9) የይሖዋ ምሥክር እንደመሆንህ መጠን ይህ ቪዲዮ የዓለም ክፍል አለመሆንን በተመለከተ ምን እንዲሰማህ ያደርጋል?
3 በጽናት ተቋቁመዋል በተባለው ቪዲዮ ላይ የቀረበው የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩት የሚያበረታታ ምሳሌ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ወጣቶች እንኳ እንደ ጽንፈኝነት፣ የእኩዮች ተጽእኖና ከሕሊና ጋር እንደተያያዙ ያሉ ክብደት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ሲያጋጥሟቸው እንዲቋቋሙ ሊረዳቸው ይችላል። በመለስተኛ ወይም በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የምትማር ወጣት ከሆንክ አስተማሪህ ቪዲዮውን ለማስተማሪያነት እንዲጠቀምበት ልትጋብዘው ትችላለህ? ምናልባት የዚህን ቪዲዮ አንድ ቅጂ ሰጥተህ በሰዎች ዘንድ እምብዛም ያልታወቀ የታሪክ ዘገባ ወይም ሥነ ምግባራዊ ትምህርት የሚገኝበት ጥናታዊ ፊልም እንደሆነ ልትገልጽላቸው ትችላለህ።
4 በጽናት ተቋቁመዋል የተባለው ይህ ቪዲዮ መለኮታዊ ትምህርት ትክክል ለሆነው ነገር ጽኑ አቋም በመያዝ አምላክን ለማስደሰት እንድንችል የሚያደርግ መንፈሳዊ ጥንካሬ እንደሚሰጠን የሚያሳይ ግሩም መሣሪያ ነው። (1 ቆሮ. 16:13) ለእውነት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ሁሉ እንዲያዩት አድርግ።