አገልግሎታችሁን በተሟላ ሁኔታ እየፈጸማችሁ ነውን?
1 የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ‘የተሟላ ምሥክርነት’ በመስጠት አገልግሎታቸውን መፈጸማቸውን ይገልጻል። (ሥራ 2:40 NW ፤ 8:25፤ 28:23) ሐዋርያው ጳውሎስም ይህ ግብ እንደነበረው እሙን ነው። (ሥራ 20:24 NW) የምስራቹ አገልጋዮች እንደመሆናችሁ መጠን የእናንተስ ግብ ይህ አይደለምን? ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?
2 አቀራረባችሁን ተዘጋጁ፦ በአገልግሎቱ ውጤታማ ምስክርነት ለመስጠት ዝግጅት ወሳኝ ነው። መጽሔቶቻችን በየጊዜው የተለያየ ርዕሰ ጉዳይ ይዘው ስለሚወጡ በተለይ መጽሔት ስናበረክት አስቀድመን ዝግጅት ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። ይበልጥ የታጠቅን እንድንሆን ለማገዝ ይህ የመንግሥት አገልግሎታችን እትም አዲስ አቀራረብ ይዞ ወጥቷል። በስተ ግራ ባለው ዓምድ ላይ አዲስ የወጡ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶችን ለማበርከት የሚያስችሉ የናሙና አቀራረቦች እናገኛለን። በእያንዳንዱ እትም ላይ የብዙ ሰዎችን ስሜት ሊቀሰቅስ የሚችል ወቅታዊ የሆነ ርዕሰ ጉዳይ ይጎላል። እነዚህን አጭር አቀራረቦች እንዴት ልትጠቀምባቸው ትችላለህ?
3 በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ይበልጥ ውጤታማ ይሆናል የምትለውን አቀራረብ ምረጥ። ሐሳቡ የተወሰደበትን ጽሑፍ በጥንቃቄ አንብብና ስሜት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ የተወሰኑ ነጥቦችን በማስታወሻ ያዝ። በመጽሔቱ ውስጥ የተጠቀሰ ለውይይቱ ተስማሚ የሆነና ለቤቱ ባለቤት ልታነብለት የምትችለው አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ምረጥ። የምታነጋግረው ሰው መጽሔቱን እንዲያነበው የሚያበረታታ አጠር ያለ መደምደሚያና ለዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ አስተዋጽዎ ማድረግ እንደሚችል የሚጠቁም ሐሳብ አክልበት። አሁን አቀራረብህን ተለማመደው።
4 መጽሐፍ ቅዱስን ለመጠቀም ግብ አድርግ፦ በሚገባ ከታሰበበት በአቀራረብህ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ መጨመር ይቻላል። ለምሳሌ በብዙ አካባቢዎች የሚገኙ ተሞክሮ ያላቸው አስፋፊዎች መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ለቤቱ ባለቤት ሰላምታ ከሰጡ በኋላ የሚከተለውን አቀራረብ በመጠቀማቸው ውጤት አግኝተዋል:-
“ሰዎች በሚከተለው አባባል ያምኑ እንደሆነ እየጠየቅናቸው ነበር።” ዘፍጥረት 1:1ን አንብብና “እርስዎ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ?” ብለህ ጠይቀው። የሚስማማ ከሆነ እንዲህ በል:- “እኔም እስማማለሁ። ይሁን እንጂ ሁሉንም ነገር የፈጠረው እግዚአብሔር ከሆነ ለክፋትም ተጠያቂው እርሱ ነው ብለው ያስባሉ?” የሰውዬውን ምላሽ ካዳመጥክ በኋላ መክብብ 7:29ን አንብብ። ከዚያም ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 99 ግለጥና አንቀጽ 1ን አንብብ። ሰውዬው መጽሐፉን ወስዶ እንዲያነበው ሐሳብ አቅርብለት። ነገር ግን የቤቱ ባለቤት ዘፍጥረት 1:1 ላይ ባለው ሐሳብ የማይስማማ ከሆነ ለዘላለም መኖር ከተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 4ን እንዲመረምር አበረታታው።
5 ፍላጎት ያሳዩትን ሁሉ ተከታትላችሁ እርዱ፦ ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች ተከታትላችሁ ካልረዳችሁ አገልግሎታችሁን በተሟላ ሁኔታ ልትፈጽሙ አትችሉም። መጽሔት ወይም ሌላ ጽሑፍ አበረከታችሁም አላበረከታችሁ ከሰውዬው ጋር ጥሩ ውይይት ካደረጋችሁ የግለሰቡን ስምና አድራሻ መዝግባችሁ ያዙ። ሳትዘገዩ ተመልሳችሁ በመሄድ የሰውዬውን ፍላጎት ለማሳደግ ሞክሩ። መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና መጋበዝ አትርሱ።
6 የመጀመሪያው መቶ ዘመን ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ‘የተሟላ ምስክርነት እንዲሰጡ’ እንዳዘዛቸው ያውቁ ነበር። (ሥራ 10:42 NW) ደቀ መዛሙርት ለማድረግ የሚያስችለን ብቸኛው መንገድ ስለሆነ ይህ ትእዛዝ ለእኛም ይሠራል። (ማቴ. 28:19, 20) አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም እንድንችል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናድርግ።—2 ጢሞ. 4:5