ከስብከቱ ሥራ የምታገኙት ደስታ እየጨመረ ይሂድ
1 ምሥራቹን ለሌሎች በማካፈል የሚገኘውን ደስታ በአገልግሎትህ እየቀመስከው ነውን? ካልተጠነቀቅን በዙሪያችን ያለው ክፉ ዓለም መስበክ እንዲያስፈራንና በዚህም ምክንያት ደስታችንን እንድናጣ ሊያደርገን ይችላል። ፍሬ በማይገኝበት ክልል ውስጥ መሥራትም ተስፋ ሊያስቆርጠን ይችላል። በስብከቱ ሥራ የምናገኘውን ደስታ ለማሳደግ ምን ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ እንችላለን?
2 አዎንታዊ አመለካከት ይኑራችሁ፦ አዎንታዊ አመለካከት መያዝ በጣም ጠቃሚ ነው። ይህንን ማድረግ የምንችልበት አንደኛው መንገድ ‘ከአምላክ ጋር አብረን ለመሥራት’ ባገኘነው ታላቅ መብት ላይ ማሰላሰል ነው። (1 ቆሮ. 3:9) ይህንን ሥራ በማከናወን ረገድ ኢየሱስም አብሮን ነው። (ማቴ. 28:20) በመላእክት ሠራዊት ይደግፈናል። (ማቴ. 13:41, 49) እንግዲያው የምናደርገው ጥረት መለኮታዊ አመራር እንዳለው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ራእይ 14:6, 7) ስለዚህ አንዳንድ ሰዎች ለሥራችን የሚሰጡት ምላሽ ምንም ዓይነት ቢሆን በሰማይ ያሉት በላቀ ሁኔታ ይደሰታሉ!
3 በሚገባ ተዘጋጁ፦ ጥሩ ዝግጅት ማድረግም ለደስታችን አስተዋጽዎ ያደርጋል። ለአገልግሎት መዘጋጀት ብዙ ሥራ የሚጠይቅ አይደለም። በወቅቱ ከወጡት መጽሔቶች ወይም በወሩ ከሚበረከቱት ጽሑፎች ለመወያያ የሚሆን ነጥብ ለመመልከት ጥቂት ደቂቃ በቂ ነው። በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ “መጽሔቶችን ለማበርከት ምን ማለት ይቻላል?” ከሚለው ርዕስ አንድ መግቢያ ምረጡ። “ለመስክ አገልግሎት የሚሆኑ አቀራረቦች” የሚለውን የጥር 2002 አባሪ ተመልከቱ ወይም ውጤታማ የሆነ መግቢያ ለማግኘት የማመራመር መጽሐፍን ተመልከቱ። የቤት ባለቤቶች አዘውትረው የሚያነሱት ተቃውሞ ዕንቅፋት ከሆነብህ የሚሰነዝሩትን አስተያየት የሚያረግብና ፍላጎታቸውን ለውይይት የሚያነሳሳ ምላሽ አዘጋጅ። በዚህ ረገድ የማመራመር መጽሐፍ ከፍተኛ እርዳታ ያበረክታል። በእነዚህ መሣሪያዎች መጠቀማችን ደስተኛ ሆነን ለመስበክ የሚያስፈልገንን ድፍረት ይሰጠናል።
4 አጥብቃችሁ ጸልዩ፦ ዘላቂ የሆነ ደስታ ለማግኘት ጸሎት አስፈላጊ ነው። የምንሠራው የይሖዋን ሥራ እንደመሆኑ መጠን መንፈሱን እንዲሰጠን መለመን ያስፈልገናል። መንፈሱ ከሚያፈራቸው ፍሬዎች መካከል አንዱ ደስታ ነው። (ገላ. 5:22) ይሖዋ መስበካችንን እንድንቀጥል የሚያስፈልገንን ጥንካሬ ይሰጠናል። (ፊልጵ. 4:13) ስለ አገልግሎታችን መጸለይ ደስ የማያሰኙ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ ትክክለኛ አመለካከት ይዘን እንድንቀጥል ይረዳናል። (ሥራ 13:52፤ 1 ጴጥ. 4:13, 14) ጸሎት ፍርሃት ሲሰማን ደፋሮችና ደስተኞች ሆነን ለመቀጠል ያስችለናል።—ሥራ 4:31
5 አጋጣሚዎችን ፈልጉ፦ እርግጥ ነው፣ አገልግሎታችን ይበልጥ አስደሳች የሚሆነው ሰዎችን ማግኘት ስንችልና ስንመሰክርላቸው ነው። ከቤት ወደ ቤት የምታገለግሉበትን ሰዓት በመለዋወጥ ምናልባትም ከሰዓት በኋላ ወይም አመሻሹ ላይ ማድረግ የተሻለ ውጤት ያስገኝላችሁ ይሆናል። በመንገድ ላይ ስትሄዱ፣ ወደ ገበያ ስትወጡ፣ በአውቶቡስ ተሳፍራችሁ ስትሄዱ፣ ወይም በመናፈሻ ቦታ ስትዝናኑ ሰዎችን ታገኛላችሁ። በቀላሉ ውይይት ለመጀመር የሚያስችል አጭር ሐሳብ ተዘጋጅታችሁ ወዳጃዊ መንፈስ ያላቸውን ሰዎች ቅድሚያውን ወስዳችሁ ለምን አታነጋግሯቸውም? ወይም ደግሞ በሥራ ቦታ አሊያም በትምህርት ቤታችሁ በየዕለቱ ከሰዎች ጋር የመነጋገር አጋጣሚ ይኖራችሁ ይሆናል። ፍላጎት የሚቀሰቅስ አንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ በማንሳት ብቻ ምሥክርነት ለመሥጠት የሚያስችል አጋጣሚ ታገኙ ይሆናል። የጥር 2002 የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ የመጀመሪያ ገጽ ላይ ግሩም የሆኑ ሐሳቦችን ማግኘት ይቻላል። ከእነዚህ መንገዶች በአንዱ ለመሥራት ጥረት ማድረጋችን በስብከቱ ሥራ የምናገኘውን ደስታ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽዎ ያደርጋል።
6 ደስታ ለመጽናት ስለሚያስችለን ደስተኞች ሆነን መኖራችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! እንደዚህ በማድረግ ይህ ፈጽሞ የማይደገም ሥራ ሲጠናቀቅ የተትረፈረፈ በረከት እናጭዳለን። ይህ ተስፋ ራሱ በስብከቱ ሥራ የምናገኘውን ደስታ ሊጨምርልን ይችላል።—ማቴ. 25:21