“ይሖዋን በደስታ አገልግሉት”
1. የይሖዋ አገልጋዮች ምን አስደሳች መብት አላቸው?
1 ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፣ ደስ ይበላችሁ” በማለት ጽፏል። (ፊልጵ. 4:4) ምስራቹን ለመስበክና በግ መሰል ሰዎች ይሖዋን እንዲያመልኩ ለመርዳት ያገኘነው መብት በጣም አስደሳች ነው። (ሉቃስ 10:17፤ ሥራ 15:3፤ 1 ተሰ. 2:19) ሆኖም አንዳንድ ጊዜ በአገልግሎታችን ደስተኞች እንዳልሆንን የሚሰማን ከሆነ ምን ማድረግ እንችላለን?
2. ተልእኳችንን የሰጠን ማን እንደሆነ ማስታወሳችን ደስተኞች እንድንሆን አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?
2 ከአምላክ የተሰጠን ሥራ:- የስብከት ተልእኳችንን የሰጠን ይሖዋ መሆኑን አትዘንጉ። የመንግሥቱን መልእክት በማወጅና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ “[ከእግዚአብሔር] ጋር አብረን የምንሠራ” መሆናችን እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው! (1 ቆሮ. 3:9) በዚህ ፈጽሞ በማይደገም ሥራ ኢየሱስ ክርስቶስም አብሮን ይሠራል። (ማቴ. 28:18-20) መላእክትም እንዲሁ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ባለው ታላቅ መንፈሳዊ የመከር ሥራ በትጋት የሚካፈሉ ከመሆኑም በላይ ከእኛ ጋር እየሠሩ ናቸው። (ሥራ 8:26፤ ራእይ 14:6) ቅዱሳን ጽሑፎችና የአምላክ ሕዝቦች ከዚህ ቀደም ያጋጠሟቸው ተሞክሮዎች በግልጽ እንደሚያሳዩት አምላክ ሥራውን እየደገፈው ነው። በመሆኑም በስብከቱ ሥራ በምንካፈልበት ጊዜ “ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።” (2 ቆሮ. 2:17) ደስተኞች ሆነን እንድናገለግል የሚገፋፋ ግሩም ምክንያት አለን!
3. በአገልግሎታችን ደስተኞች ሆነን እንድንቀጥል በመርዳት ረገድ ጸሎት ምን ድርሻ ያበረክታል?
3 በአምላክ አገልግሎት ደስታችንን ጠብቀን ለመመላለስ ጸሎት አስፈላጊ ነው። (ገላ. 5:22) የአምላክን ሥራ ማከናወን የምንችለው ከእርሱ በምናገኘው ኃይል ብቻ በመሆኑ ለሚጠይቁት አብዝቶ የሚለግሰውን መንፈሱን እንዲሰጠን አጥብቀን ልንለምነው ይገባል። (ሉቃስ 11:13፤ 2 ቆሮ. 4:1, 7፤ ኤፌ. 6:18-20) ስለ አገልግሎታችን መጸለያችን አሉታዊ ምላሽ በሚያጋጥመን ጊዜ ትክክለኛውን አመለካከት እንድንይዝ ይረዳናል። በድፍረትና በደስታ መስበካችንን እንድንቀጥልም ያስችለናል።—ሥራ 4:29–31፤ 5:40-42፤ 13:50-52
4. በሚገባ መዘጋጀታችን በስብከቱ ሥራ የምናገኘውን ደስታ ለማሳደግ የሚረዳን እንዴት ነው? ዝግጅት ለማድረግ የሚረዱ አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
4 በሚገባ ተዘጋጁ:- በአገልግሎት ስንካፈል ደስታችንን ከፍ ለማድረግ የሚረዳን አንዱ መንገድ በሚገባ መዘጋጀት ነው። (1 ጴጥ. 3:15) እንደዚህ ያለውን ዝግጅት ለማድረግ ረጅም ሰዓት ላያስፈልገን ይችላል። በወቅቱ ለሚበረከቱት መጽሔቶች የወጡትን የመግቢያ ሐሳቦች መመልከት ወይም ልታበረክቱ ላሰባችሁት ጽሑፍ የሚስማማ መግቢያ መዘጋጀት ከጥቂት ደቂቃዎች በላይ አይፈጅም። ተስማሚ የሆነ መግቢያ ለማግኘት ማመራመር የተባለውን መጽሐፍ ወይም ከዚህ ቀደም የወጡ የመንግሥት አገልግሎታችን እትሞችን መመልከት ትችላላችሁ። አንዳንድ የመንግሥቱ አስፋፊዎች አጠር ያሉ የመግቢያ ሐሳቦችን በትንሽ ወረቀት ላይ ጽፎ መያዙን ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። መግቢያቸውን ለማስታወስ አልፎ አልፎ ወረቀቱን አየት ያደርጋሉ። እንደዚህ ማድረጋቸው ፍርሃታቸውን ለማሸነፍና በልበ ሙሉነት ለመስበክ ያስችላቸዋል።
5. ደስታ እኛንም ሆነ ሌሎችን የሚጠቅመው እንዴት ነው?
5 ደስተኞች መሆናችን ብዙ ጥቅሞች አሉት። አቀራረባችን ደስታ የተሞላበት መሆኑ መልእክታችን ማራኪ እንዲሆን ያደርጋል። ደስታ ለመጽናት እንድንችል ያጠነክረናል። (ነህ. 8:10፤ ዕብ. 12:2) ከሁሉ በላይ ደግሞ በደስታ የምናቀርበው አገልግሎት ለይሖዋ ውዳሴ ያመጣል። እንግዲያው ‘ይሖዋን በደስታ እናገልግለው።’—መዝ. 100:2 NW