አዲስ የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም
1 በዚህ ተለዋዋጭ በሆነ ዓለም ውስጥ በእምነት ጸንተን ለመቆም እንድንችል በይሖዋ መታመን አለብን። በይሖዋ መታመን ሲባል ምን ማለት ነው? በይሖዋ መታመናችን የእኛንም ሆነ የቤተሰባችንን ሕይወት የሚነካው እንዴት ነው? የሰይጣን ዓለም የሚያሳድርብንን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚረዳንስ እንዴት ነው? በ2003 የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም ላይ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን። የስብሰባው ጭብጥ “በይሖዋ ታመኑ፣ መልካምም አድርጉ” የሚል ነው።—መዝ. 37:3 NW
2 በይሖዋ የምንታመን መሆናችንን የምናሳየው አንዳንድ የተለዩ ወይም አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ ብቻ አይደለም። በዕለት ተዕለት ሕይወታችንም በይሖዋ እንደምንታመን ልናሳይ ይገባል። “ሁልጊዜ በይሖዋ ታመኑ” የሚለው የመክፈቻ ንግግር ይህንን የሚያጎላ ይሆናል። (መዝ. 62:8) “በይሖዋ የምንታመን መሆናችንን ማሳየት” በሚል ርዕስ የሚቀርበው ባለ አራት ክፍል ሲምፖዚየም የተሳካ ትዳር ለመመሥረት፣ በቤተሰብ ክልል ውስጥ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታትና ቁሳዊ ፍላጎቶቻችንን ለማሟላት እንድንችል የሚረዱንን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች እንዴት መርምረን ማግኘትና በሥራ ላይ ማዋል እንደምንችል ያሳየናል።
3 የሰይጣን ዓለም ትክክልና ስህተት የሆኑ ነገሮችን በሚመለከት የተዛባ አመለካከት እንድንይዝ ለማድረግ የሚሞክር ከመሆኑም በላይ ለምን ነገሮች ቅድሚያ መስጠት እንዳለብን ግራ እንዲገባን ያደርጋል። (ኢሳ. 5:20) “ከንቱ የሕይወት ግቦችን ከማሳደድ ተጠበቁ” እና “ከክፉ ራቁ—መልካሙን የምታደርጉ ሁኑ” የሚሉት ንግግሮች የይሖዋን የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ለማክበር የገባነውን ቁርጥ አቋም ያጠናክሩልናል።—አሞጽ 5:14
4 ይሖዋ በጊዜያችን ያለውን ክፉ ሥርዓት በሚያጠፋበት ወቅት አገልጋዮቹ በእርሱ ሙሉ በሙሉ መታመን ያስፈልጋቸዋል። “ከዓለም መከራ ነጻ የምንወጣበት ጊዜ ቀርቧል” በሚል ርዕስ የሚቀርበው የሕዝብ ንግግር ይህንን ያብራራል። ከዚያም “የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለመሆን ትበቁ ይሆን?” የሚለው ንግግር ራሳችንን እንድንመረምር ግብዣ ያቀርብልናል። በመጨረሻም ስብሰባው “ይሖዋ በገባቸው ተስፋዎች ላይ እምነት ይኑራችሁ” የሚል ጥብቅ ማሳሰቢያ በያዘ ንግግር ይደመደማል።
5 በሁሉም ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ጎላ ያለ ቦታ ከሚሰጣቸው ንግግሮች አንዱ የጥምቀት ንግግር ነው። ለመጠመቅ የሚፈልጉ ሁሉ ከአሁኑ አስፈላጊውን ዝግጅቶች ማድረግ ይቻል ዘንድ ለጉባኤያቸው ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች በተቻለ ፍጥነት ማሳወቅ ይኖርባቸዋል።
6 በዚህ አስተማማኝ ባልሆነ ጊዜ ትምክህት ሊጣልበት የሚችለውና ጽኑ መታመኛ የሆነው ይሖዋ ብቻ ነው። (መዝ. 118:8, 9) ሁላችንም ከወረዳ ስብሰባው ፕሮግራም አንዱም እንዳያመልጠን በማድረግ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት እናጠናክር።