አዲስ የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም
ይሖዋ ልናፈቅረውና ለእርሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ ልናቀርብለት የሚገባው አምላክ እንደሆነ እናውቃለን። ይሁን እንጂ ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን የጠበቀ ወዳጅነት እንድናላላ ዓለም ሊያታልለን ይፈልጋል። (ዮሐ. 17:14) ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ለማጠንከርና በመንፈሳዊነታችን ላይ አደጋ የሚጥሉትን የዓለም ነገሮች እንድናሸንፍ ብርታት ለመስጠት የ2001 የአገልግሎት ዓመት አዲስ የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም “አምላክን እንጂ በዓለም ያሉትን ነገሮች አትውደዱ” በሚል ጭብጥ ተዘጋጅቷል።—1 ዮሐ. 2:15-17
ለይሖዋ ያለን ጥልቅ ፍቅር ስለ እርሱ እንድንመሠክር ይገፋፋናል። ያም ሆኖ ለብዙዎቹ የአምላክ ሕዝቦች የመስክ አገልግሎት እንዲህ ቀላል አይደለም። “ለአምላክ ያለን ፍቅር እንድናገለግል ይገፋፋናል” የሚለው ንግግር ብዙዎች በዚህ ሥራ ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ ዓይናፋርነትንና ሌሎች መሰናክሎችን እንዴት እንዳሸነፉ እንማራለን።
እያዘቀጠ የመጣው የዓለም የሥነ ምግባር ደረጃ ተጽዕኖ የሚያሳድርብን እንዴት ነው? በአንድ ወቅት እንደ ነውር ይታዩ የነበሩ ሁኔታዎች አሁን የተለመዱ ሆነዋል። “ይሖዋን የሚወዱ ክፋትን ይጠላሉ” የሚለው ንግግርና “በዓለም ላሉ ነገሮች ያለን አመለካከት ምንድን ነው?” በሚል ርዕስ የሚቀርበው ሲምፖዚየም መጥፎ ምኞቶችን እምቢ ለማለት ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል።
ፕሮግራሙ የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት እና የአገልግሎት ስብሰባ ናሙናዎችን የሚያካትት ሲሆን የሳምንቱ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት በክለሳ ይቀርባል። “ፍቅርና እምነት ዓለምን የሚያሸንፉት እንዴት ነው?” በሚል ርዕስ የሚቀርበው የሕዝብ ንግግር ዓለማዊ ተጽዕኖዎችን በመቋቋም ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ እንድንኮርጅ ማበረታቻ ይሰጠናል። (ዮሐ. 16:33) ጥናቶችህ በስብሰባው ላይ እንዲገኙ መጋበዝ አትርሳ። አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶችን ማድረግ እንዲቻል መጠመቅ የሚፈልጉ ሁሉ በተቻለ መጠን ቀደም ብለው ለሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ መንገር ይገባቸዋል።
ይሖዋ የሚያመጣውን ታላቅ በረከት ለማጣጣም ፍቅራችን የት ቦታ ላይ ማረፍ እንዳለበት ትኩረት እንድናደርግ ይህ የወረዳ ስብሰባ ይረዳናል። የትኛውም የስብሰባው ክፍል እንዳያመልጥህ!