ለክርስቲያን አገልጋዮች የተደረገ ዝግጅት
1. በ1938 ምን አዲስ ዝግጅት ተጀመረ? ዓላማውስ ምን ነበር?
1 በ1938 የይሖዋ ድርጅት አንድ አዲስ ዝግጅት እንዲጀመር አደረገ። ጉባኤዎች በቡድን በቡድን ሆነው በአሁኑ ጊዜ የወረዳ ስብሰባዎች ተብለው በሚጠሩት የዞን ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ተጋብዘው ነበር። ዓላማው ምን ነበር? የጥር 1939 የኢንፎርማንት እትም (በአሁኑ ጊዜ የመንግሥት አገልግሎታችን ይባላል) እንዲህ የሚል መልስ ሰጥቶ ነበር፦ “እነዚህ ትልልቅ ስብሰባዎች ይሖዋ የመንግሥቱን አገልግሎት ለማካሄድ የሚጠቀምባቸው የቲኦክራሲያዊ ድርጅቱ ክፍል ናቸው። በስብሰባዎቹ ላይ የሚቀርበው ትምህርት እያንዳንዱ ሰው የተሰጠውን ሥራ በተገቢው መንገድ እንዲያከናውን ያስችለዋል።” የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር በ1938 ከነበረው ከ58,000 ተነስቶ በ2009 ከ7,000,000 በላይ መድረሱን ስንመለከት የወረዳ ስብሰባዎች ዓላማቸውን እንዳከናወኑ ማለትም የመንግሥቱ አገልጋዮች ‘የተሰጣቸውን ሥራ’ እንዲፈጽሙ እንዳስቻሉ በግልጽ መገንዘብ እንችላለን!
2. በአዲሱ የአገልግሎት ዓመት በወረዳ ስብሰባ ላይ የትኞቹ ንግግሮች ይቀርባሉ?
2 የቀጣዩ ዓመት ጭብጥ፦ ከመስከረም ወር ጀምሮ የሚካሄደውን የወረዳ ስብሰባና በስብሰባው ላይ የምናገኘውን ማበረታቻ በጉጉት እንጠባበቃለን። ‘የዓለም ክፍል አይደላችሁም’ የሚለው የስብሰባው ጭብጥ የተወሰደው ከዮሐንስ 15:19 ላይ ነው። በስብሰባው ላይ ከሚቀርቡት ክርስቲያን አገልጋዮችን ከሚጠቅሙ ንግግሮች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው? ቅዳሜ ዕለት “የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጥበቃ ይሆንልናል—እንዴት?” የሚል ንግግር ይቀርብልናል። በተጨማሪም “በአውሬው እንዳትረክሱ ተጠንቀቁ፣” “በታላቂቱ ጋለሞታ እንዳትረክሱ ተጠንቀቁ” እና “በተጓዥ ነጋዴዎች እንዳትረክሱ ተጠንቀቁ” የሚሉ ሦስት ንግግሮች ያሉት ሲምፖዚየም ይቀርብልናል። እሁድ ዕለት ደግሞ “ዓለምን ሳይሆን ይሖዋን ውደዱ” የሚል ጭብጥ ያለው ሲምፖዚየም ይቀርባል። እንዲሁም በዚያ ዕለት “‘መጻተኞችና ጊዜያዊ ነዋሪዎች’ ሆናችሁ ቀጥሉ” እና “አይዟችሁ! ዓለምን ልታሸንፉ ትችላላችሁ” የሚሉ ሌሎች ንግግሮችም ይቀርባሉ።
3. በወረዳ ስብሰባ ላይ መገኘታችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
3 በአገልግሎት የምታደርገውን እንቅስቃሴ ቀንሳ የነበረች አንዲት እህት በቅርቡ በተደረገ የወረዳ ስብሰባ ላይ ከተገኘች በኋላ ስብሰባው ያለችበትን ሁኔታ እንደገና እንድትመረምርና ‘አገልግሎት ላለመውጣት ሰበብ መደርደሯን እንድታቆም’ እንደረዳት ጽፋለች። በአዲሱ የአገልግሎት ዓመት የሚደረገው የወረዳ ስብሰባ ሁላችንም ዓለምን ሳይሆን ይሖዋን እንድንወድ እንደሚረዳን ምንም ጥርጥር የለውም። (1 ዮሐ. 2:15-17) አንተም ለክርስቲያን አገልጋዮች ከተደረገው ከዚህ ፍቅራዊ ዝግጅት መጠቀም እንድትችል በስብሰባው ላይ ለመገኘትና ትምህርቱን በትኩረት ለመከታተል ጥረት አድርግ!