አዲስ የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም
መጽሐፍ ቅዱስ “የሚያስጨንቅ ጊዜ” ብሎ በሚጠራው በዚህ ዘመን የይሖዋን ሞገስ አግኝተን ለመኖር አምላካዊ ጥበብ ያስፈልገናል። (2 ጢሞ. 3:1) “‘ከሰማይ በሆነችው ጥበብ’ ተመሩ” በሚል ጭብጥ የተዘጋጀው የ2005 የአገልግሎት ዓመት የወረዳ ስብሰባ ተግባራዊ ልናደርገው የምንችለው ምክርና ማበረታቻ ይሰጠናል።—ያዕ. 3:17
በስብሰባው ላይ ከሚቀርቡት ተከታታይ ንግግሮች የመጀመሪያው “‘ከሰማይ የሆነችውን ጥበብ’ በሕይወታችን ውስጥ ማንጸባረቅ” የሚል ጭብጥ ያለው ሲሆን ንጹሕ፣ ሰላም ወዳድ፣ ምክንያታዊና እሺ ባይ መሆን ምን ነገሮችን እንደሚያካትት እንድንገነዘብ ይረዳናል። ቀጥሎም የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ሌሎቹን ሦስት የአምላክ ጥበብ ገጽታዎች ያብራራል። የአውራጃ የበላይ ተመልካቹ፣ ክርስቲያን ሰባኪዎች በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ “ያልተማሩ ተራ ሰዎች” እንደሆኑ ተደርገው ቢታዩም የአምላክን ጥበብ ለመናገር ብቁ የሚሆኑበትን ምክንያት በማብራራት የመጀመሪያውን ዕለት ስብሰባ ይደመድማል።—ሥራ 4:13
በሁለተኛው ቀን “የሚያንጹ ነገሮችን ተከታተሉ” በሚል ጭብጥ የሚቀርቡት ተከታታይ ንግግሮች መንፈሳዊነታችንን ሊያዳክሙ የሚችሉ ነገሮችን ለማወቅና ለማስወገድ እንድንችል ያስታጥቁናል። ከዚህም በላይ በጉባኤ ስብሰባዎች፣ በመስክ አገልግሎትና በቤተሰባችን ውስጥ ሌሎችን እንዴት ማነጽ እንደምንችል ያስገነዝቡናል። “ከአምላካዊ ጥበብ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?” የሚል ርዕስ ያለው የሕዝብ ንግግር አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ በማድረጋችን ለምናገኛቸው በረከቶች ጥልቅ አድናቆት እንዲያድርብን ያደርገናል። የመደምደሚያው ንግግር “ከሰማይ በሆነችው ጥበብ መመራት ከክፉ ይጠብቀናል” የሚል ሲሆን በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የይሖዋን ጥበብ ለመሻት ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል።
በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ክንውኖች አንዱ የአዳዲስ ደቀ መዛሙርት ጥምቀት ነው። በዚያ ሳምንት የሚደረገው የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤትና የመጠበቂያ ግንብ ጥናትም በስብሰባው ላይ ይቀርባል። ይሖዋ ሁላችንም እርሱ ከሚሰጠው ጥበብ ተጠቃሚዎች እንድንሆን ይፈልጋል። በወረዳ ስብሰባችን ላይ የሚሰጠን ምክርና ማበረታቻ በመንፈሳዊ የሚያበለጽገን ይሆናል።—ምሳሌ 3:13-18