መንፈሳዊነታችንን እንድንጠብቅ የሚረዳን የወረዳ ስብሰባ
1. ይሖዋ ምሥራቹን እንድናስፋፋ የተሰጠንን ተልእኮ እንድንወጣ ለመርዳት ካደረጋቸው ዝግጅቶች መካከል አንዱ ምንድን ነው?
1 ይሖዋ ምሥራቹን እንድናስፋፋ የተሰጠንን መለኮታዊ ተልእኮ እንድንወጣ ለመርዳት አስፈላጊውን ትምህርት፣ ሥልጠናና ማበረታቻ አትረፍርፎ ይሰጠናል። (ማቴ. 24:14፤ 2 ጢሞ. 4:17) እንዲህ ያለውን እርዳታ ከምናገኝባቸው ዝግጅቶች አንዱ በየዓመቱ የምናደርገው የወረዳ ስብሰባ ነው። በ2010 የአገልግሎት ዓመት የምናደርገው አዲስ የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም “መንፈሳዊነታችሁን ጠብቁ” የሚለውን ጭብጥ የሚያብራራ ሲሆን በሮም 8:5 እና በይሁዳ 17-19 ላይ የተመሠረተ ነው። በዓለም ዙሪያ የሚካሄደው ይህ ፕሮግራም ነሐሴ 31, 2009 ከሚጀምረው ሳምንት አንስቶ ይቀርባል።
2. (ሀ) የወረዳ ስብሰባው ጥቅም የሚያስገኝልን በምን መንገዶች ነው? (ለ) ከዚህ ቀደም የተካሄዱት የወረዳ ስብሰባዎች በአገልግሎት ረገድ የረዷችሁ እንዴት ነው?
2 ከወረዳ ስብሰባው የምናገኛቸው ጥቅሞች፦ ፕሮግራሙ ጊዜያችንን ከሚሻሙና ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዳናተኩር ከሚያደርጉ ነገሮችም ሆነ እነዚህን ከመሳሰሉ ሌሎች አደገኛ ሁኔታዎች እንድንጠበቅ ያስጠነቅቀናል። በተጨማሪም የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን በሚመለከት የተለሳለሰ አቋም ላለመያዝ ምን ማድረግ እንዳለብን እንዲሁም አንድን ግለሰብ መንፈሳዊ ሰው የሚያስብለው ምን እንደሆነ እንማራለን። እሁድ የሚቀርበው ሲምፖዚየም ደግሞ ጫናዎችና ከባድ የእምነት ፈተናዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ በመጡበት በዚህ ጊዜ ግለሰቦችም ሆኑ ቤተሰቦች መንፈሳዊነታቸውን ለማጠናከር ምን እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚችሉ ያብራራል። ፕሮግራሙ ልባችንንም ሆነ መንፈሳዊ ጤንነታችንን እንድንጠብቅ እንዲሁም መንፈሳዊነታቸውን የሚጠብቁ ሰዎች ወደፊት የሚያገኙት ታላቅ በረከት ግልጽ ሆኖ በዓይነ ሕሊናችን እንዲታየን ይረዳናል።
3. ቀጣዩ የወረዳ ስብሰባችሁን የምታደርጉት መቼ ነው? ቁርጥ ውሳኔያችሁስ ምን መሆን አለበት?
3 ጉባኤያችሁ የወረዳ ስብሰባውን የሚያደርገው መቼ እና የት እንደሆነ እንዳወቃችሁ ሁለቱንም ቀናት ጠዋትም ሆነ ከሰዓት ለመገኘትና ትምህርቶቹን በጥሞና ለመከታተል ከወዲሁ እቅድ አውጡ። ይሖዋ ትጉህ የሆኑ ሰዎችን ጥረት እንደሚባርክ እርግጠኞች ሁኑ።—ምሳሌ 21:5
4. በቀጣዩ የወረዳ ስብሰባችን ምን ነገር እንደምናገኝ እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
4 በእርግጥም የዚህ መልካም ስጦታ ምንጭ ይሖዋ ነው። ታማኙ ባሪያ በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት ክርስቲያን አገልጋዮች ሆነን ለመቀጠል የሚያስፈልገንን ነገር አቅርቦልናል። “ተስፋችንን በይፋ ለማወጅ የሚያስችለንን አጋጣሚ ያላንዳች ማወላወል አጥብቀን [እንድንይዝ]” የሚረዱንን ዝግጅቶች ሁሉ በፍቅር ስላቀረበልን ይሖዋን እናመሰግነዋለን!—ዕብ. 10:23-25፤ ያዕ. 1:17