የመንግሥት አዳራሽ ቤተ መጻሕፍትን በሚመለከት የተደረገ አዲስ ዝግጅት
ለበርካታ ዓመታት በዓለም ዙሪያ ያሉ ጉባኤዎች ቀደም ሲል የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ቤተ መጻሕፍት በሚል ስያሜ ይጠራ ከነበረው የመንግሥት አዳራሽ ቤተ መጻሕፍት በርካታ ጥቅሞች አግኝተዋል። ቀደም ባሉት ጊዜያት እያንዳንዱ ጉባኤ የራሱን ቤተ መጻሕፍት ማደራጀቱ አስፈላጊ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ ነበር። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በአንድ አዳራሽ በጋራ የሚጠቀሙ በርካታ ጉባኤዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ በውጭ አገር ቋንቋ የሚካሄዱ ናቸው። ስለዚህ በአንድ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በተመሳሳይ ቋንቋ የሚካሄዱ ጉባኤዎች በጋራ የሚጠቀሙበት በጥሩ ሁኔታ የተደራጀና የተሟላ አንድ ቤተ መጻሕፍት ብቻ ማቋቋሙ የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል። ከአንድ በላይ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ላላቸው የመንግሥት አዳራሾች ደግሞ በእያንዳንዱ አዳራሽ ውስጥ የሚሰበሰቡት ጉባኤዎች አንድ የጋራ ቤተ መጻሕፍት የሚኖራቸው ሲሆን በተለያየ ቋንቋ የሚጠቀሙ ከሆነ ደግሞ በየቋንቋው አንድ አንድ ቤተ መጻሕፍት ይኖራቸዋል።
ይህ ዝግጅት ቦታና ወጪ ይቆጥባል ተብሎ ይታሰባል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ጉባኤዎች ቤተ መጻሕፍት አንድ ላይ ሲዋሐዱ አንድ የተሻለ ቤተ መጻሕፍት እንደሚገኝ የታወቀ ነው። ቤተ መጻሕፍቱ በሚቀላቀሉበት ጊዜ ትርፍ የሆኑትን መጻሕፍት ለይቶ በማስቀመጥ ከጊዜ በኋላ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ሲሠራ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል። የመንግሥት አዳራሹ በሲዲ የተዘጋጁትን የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች የያዘ ኮምፒውተር ካለው አንዳንዶች በዚህ ጥሩ አድርገው ሊጠቀሙ ይችላሉ።
ለእያንዳንዱ ቤተ መጻሕፍት አንድ ወንድም (የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የበላይ ተመልካች ቢሆን ይመረጣል) ኃላፊ ሆኖ እንዲያገለግል ይመደባል። ይህ ወንድም በየጊዜው አስፈላጊ የሆኑ ጽሑፎችን ማሰባሰብ ያለበት ሲሆን ጽሑፎቹ የቤተ መጻሕፍቱ ንብረት መሆናቸውን ለማመልከት በሽፋኑ ውስጠኛ ክፍል በጉልህ የሚታይ ምልክት ያደርጋል። ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ከቤተ መጻሕፍቱ ምንም ጽሑፍ አለመጉደሉንና ሁሉም ጽሑፎች በጥሩ ይዞታ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ማጣራት አለበት። የቤተ መጻሕፍቱ ጽሑፎች ከመንግሥት አዳራሹ ውጪ መወሰድ አይኖርባቸውም።
የመንግሥት አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ለሁሉም የጉባኤው አባላት በረከት እንደሚሆን የታወቀ ነው። እኛ በግለሰብ ደረጃ የቤተ መጻሕፍቱን ንብረቶች በጥንቃቄ በመያዝና “የአምላክን እውቀት” ለመመርመር በዝግጅቱ በመጠቀም ልባዊ አድናቆት እንዳለን እናሳይ።—ምሳሌ 2:5