የመታሰቢያውን በዓል የሚመለከቱ ማሳሰቢያዎች
በዚህ ዓመት የመታሰቢያው በዓል የሚከበረው ረቡዕ፣ ሚያዝያ 16 ይሆናል። ሽማግሌዎች ለሚከተሉት ጉዳዮች ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል:-
◼ ስብሰባው የሚደረግበትን ሰዓት ስትወስኑ ቂጣውና ወይኑ ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት መዞር እንደሌለባቸው አስታውሱ።
◼ የሚቻል ከሆነ እያንዳንዱ ጉባኤ የመታሰቢያውን በዓል ለብቻው ቢያከብር ይመረጣል።
◼ ሊቀ መንበሩንና ተናጋሪውን ጨምሮ ሁሉም ተሰብሳቢዎች በዓሉ የሚከበርበት ትክክለኛ ጊዜና ቦታ ሊነገራቸው ይገባል።
◼ ተገቢው ዓይነት ቂጣና ወይን ተዘጋጅቶ መቀመጥ አለበት።—መጠበቂያ ግንብ የካቲት 15, 1985 ገጽ 19ን (መግ 2-106 ገጽ 17ን) እና የጥር 2003 የመንግሥት አገልግሎታችን ማስታወቂያ ተመልከቱ።
◼ ሳህኖች፣ ብርጭቆዎች እንዲሁም ተስማሚ የሆነ ጠረጴዛና የጠረጴዛ ጨርቅ ቀደም ብለው ወደ ስብሰባው አዳራሽ መጥተው በየቦታቸው መቀመጥ ይኖርባቸዋል።
◼ የመንግሥት አዳራሹም ሆነ ሌላ የመሰብሰቢያ ቦታ ቀደም ብሎ በሚገባ መጽዳት አለበት።
◼ አስተናጋጆች እንዲሁም ቂጣውንና ወይኑን የሚያዞሩ ወንድሞች ቀደም ተብሎ ሊመረጡና የሥራ ድርሻቸው፣ ተገቢ የሆነው የአሠራር ሥርዓት፣ ቂጣውና ወይኑ የሚዞሩበት መንገድ እንዲሁም ሥርዓታማ የሆነ አለባበስና አበጣጠር አስፈላጊ መሆኑ ሊነገራቸው ይገባል።
◼ አቅመ ደካማ በመሆናቸው በበዓሉ ላይ መገኘት የማይችሉ ቅቡዓን ከቂጣውና ከወይኑ መካፈል የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸት ይኖርበታል።
◼ በአንድ የመንግሥት አዳራሽ ከአንድ በላይ የሆኑ ጉባኤዎች የሚጠቀሙ ከሆነ ከአዳራሹ ውጪ አላስፈላጊ ጭንቅንቅ እንዳይፈጠር በጉባኤዎቹ መካከል ጥሩ ቅንጅት ሊኖር ይገባል። የሚቻል ከሆነ አንድ ጉባኤ በዓሉን አክብሮ ከጨረሰ በኋላ ሌላው እስኪጀምር ድረስ ከ30 እስከ 45 ደቂቃ ክፍተት መተዉ ጥሩ ይሆናል።