በቡድን ሆኖ ማገልገል ደስታ ያስገኛል
1 ኢየሱስ 70 ደቀ መዛሙርትን ለስብከት በላከበት ጊዜ ምን ብለው እንደሚናገሩ አስተምሯቸዋል፣ ሁለት ሁለት አድርጎ መድቧቸዋል እንዲሁም የሚያገለግሉበትን ክልል ነግሯቸዋል። ይህ ላገኙት ደስታ አስተዋጽኦ አበርክቷል። (ሉቃስ 10:1-17) በተመሳሳይም ዛሬ በቡድን ሆኖ ማገልገል የአምላክ ሕዝቦች ለስብከቱ ሥራ የታጠቁና የተደራጁ እንዲሆኑ እንዲሁም በሥራው በድፍረት እንዲካፈሉ ይረዳቸዋል።
2 ሽማግሌዎች ግንባር ቀደም ሁኑ:- ሽማግሌዎች ሁሉም አስፋፊዎች በስብከቱ ሥራ ቋሚ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በመርዳት ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ። ከሰኞ እስከ ዓርብ ባሉት ቀናት የአገልግሎት ዝግጅት የማድረጉ ተቀዳሚ ኃላፊነት የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ነው። ቅዳሜና እሁድ ላይ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካች የራሱን ቡድን የአገልግሎት እንቅስቃሴ የማደራጀት ኃላፊነት አለበት። ጉባኤው በአጠቃላይ ለመስክ አገልግሎት ስምሪት የሚሰበሰብ ከሆነ (ለምሳሌ ያህል ከመጠበቂያ ግንብ ጥናት በኋላ) እያንዳንዱ የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካች ለቡድኑ አባላት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል።
3 “በአገባብና በሥርዓት ይሁን”:- የመስክ አገልግሎት ስብሰባ እንዲመራ የተመደበው ወንድም በሰዓቱ መጀመርና ስብሰባውን በ10 ወይም በ15 ደቂቃ ውስጥ መጨረስ ይኖርበታል። ስብሰባውን በጸሎት ከመደምደሙ በፊት ቡድኖቹን ማቀናጀትና የሚያገለግሉበትን ክልል መደልደል ይኖርበታል። ሆኖም ይህን የሚያደርገው የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹ በማይኖርበት ጊዜ ነው። ይህ አስፋፊዎች በክልሉ ውስጥ እጅብ ብለው እንዳይሰበሰቡ ስለሚያደርግ የስብከት ሥራችንን ክብር እንዳይቀንስ ለማድረግም ያስችላል። ከዚህም ሌላ ጳውሎስ “ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን” ሲል ከሰጠው ምክር ጋር ይስማማል። (1 ቆሮ. 14:40) በመስክ አገልግሎት ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሁሉ በሰዓቱ በመድረስ፣ ስምሪቱን ከሚመራው ወንድም ጋር ሙሉ በሙሉ በመተባበርና ስብሰባው እንዳበቃ ጊዜ ሳያባክኑ ወደ ክልሉ በማምራት ለዝግጅቱ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው።
4 አንድነታችንን ማጠናከር:- በቡድን ማገልገል በጉባኤ ውስጥ ያሉትን በቅርብ ለማወቅ ግሩም አጋጣሚ ይሰጠናል። ከአንድ ሰው ጋር ለማገልገል ቀጠሮ ይዞ መምጣቱ ስህተት ባይሆንም ከሚመደብልን ከማንኛውም አስፋፊ ጋር ለማገልገል ብለን የመስክ አገልግሎት ስብሰባ ላይ መገኘትም አስደሳች ውጤት ሊኖረው ይችላል። ብዙም ከማናውቀው አስፋፊ ጋር ልንመደብና ፍቅራችንን ‘የማስፋት’ አጋጣሚ ልናገኝ እንችላለን።—2 ቆሮ. 6:11-13
5 በቡድን ሆኖ ማገልገል የሚያበረታታ ከመሆኑም በላይ ‘ለእውነት አብረን በመሥራት’ እንድንቀራረብ ያደርገናል። (3 ዮሐንስ 8) በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ የተሟላ ተሳትፎ እናድርግ!