አዲስ የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም
አደጋ ሊደርስ እንደሆነ የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ እያየን ወይም እየሰማን እርምጃ ሳንወስድ ብንቀር ከባድ ችግር እንደሚገጥመን የታወቀ ነው። ይሖዋ የሚሰጠንን መንፈሳዊ መመሪያ ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረጉ ደግሞ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። በዚህ የአገልግሎት ዓመት የምናደርገው የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም ይህንን ጉዳይ የሚያብራራ ይሆናል። ጭብጡ “እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ” ይላል።—ሉቃስ 8:18
ጎብኚ ተናጋሪው በሚያቀርበው የመጀመሪያ ንግግር ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ የመግቢያ ምዕራፎች ላይ የሚገኙት ምክሮች ዛሬ ለእኛ እንዴት እንደሚሠሩ ያብራራል። ይኸው ተናጋሪ “አምላክ የሚሰጣችሁን ትምህርት ምንጊዜም በትኩረት ተከታተሉ” በሚል ርዕስ የመደምደሚያውን ንግግር ያቀርባል። ንግግሩ በስብሰባው ላይ የተገኙት በሙሉ በእርግጥ ይሖዋን፣ ልጁንና ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ እየሰሙ መሆናቸውን እንዲመረምሩ የሚያስችል ትምህርት ይዟል።—ማቴ. 24:45 የ1954 ትርጉም
በፕሮግራሙ ላይ በተለይ ቤተሰቦችን የሚጠቅሙ በርካታ ንግግሮች ይቀርባሉ። “ትኩረታቸው ሳይሰረቅ የአምላክን ቃል የሚያዳምጡ ቤተሰቦች” የሚለው ንግግር የዚህ ዓለም ነገሮች መንፈሳዊ እድገታችንን እንዳያጓትቱት ለመከላከል ይረዳናል። ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ለመስጠት ሲሉ በሕይወታቸው ውስጥ የተለያዩ ለውጦች ያደረጉ ወንድሞች ቃለ መጠይቅ ይደረግላቸዋል። “ወጣቶች የአምላክን ቃል በትኩረት ማዳመጣቸው ጥንካሬ የሚሰጣቸው እንዴት ነው?” በሚለው ንግግር ላይ በትምህርት ቤት፣ ከእኩዮቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ወይም በአገልግሎት ላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጎን በታማኝነት ከቆሙ ወጣቶች ጋር ቃለ ምልልስ ይደረጋል። “አምላክን በማዳመጥ ትምህርት የሚቀስሙ ሕፃናት” የተባለው ንግግር የትንንሽ ልጆችን የመማር ችሎታ አሳንሰን እንዳንመለከት ያበረታታናል። ከልጆችና ከወላጆቻቸው ጋር የሚደረጉት ቃለ ምልልሶች ልጆችን ከጨቅላነታቸው ጀምሮ በይሖዋ መንገዶች ማሠልጠን ያለውን ጥቅም እንድንገነዘብ ይረዱናል።
ሰይጣን ‘ዓለምን ሁሉ እያሳተ’ ቢሆንም ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ ሊሄዱበት የሚገባውን መንገድ እያሳያቸው ነው። (ራእይ 12:9፤ ኢሳ. 30:21) እርሱ የሚሰጠንን ምክር በጥሞና ማዳመጣችንና ታዛዥ በመሆን ምክሩን በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ማድረጋችን ጥበበኞችና ደስተኞች የሚያደርገን ከመሆኑም በላይ ዘላለማዊ ሕይወት ያስገኝልናል።—ምሳሌ 8:32-35