ከደም እንድንርቅ ለመርዳት የተደረገ አዲስ ዝግጅት
የአስተዳደር አካሉ ስለ ሕክምና ያለኝ የግል አቋም እና የሕክምና አሰጣጥን የሚመለከት ማሳሰቢያ/ባለሞያዎችን ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርግ ሰነድ በተባሉት መመሪያዎች ላይ የሚገኙትን ዋና ዋና ሐሳቦች በአንድ ላይ በማቀናጀት የሕክምና መመሪያ ካርድ ብለን የምንጠራውን አንድ ሰነድ ለማዘጋጀት የቀረበለትን ሐሳብ አጽድቋል።
ይህ የሕክምና መመሪያ ካርድ በየጊዜው መታደስ የማያስፈልገው ከመሆኑም በላይ በዓለም ዙሪያ ወደየትኛውም ቦታ ብንጓዝ ስለ ሕክምና ያለንን አቋም ለመግለጽ ያገለግላል። ወደፊት አዲስ የሕክምና መመሪያ መሙላት የሚያስፈልገን (1) ስለ ሕክምና ያለንን አቋም፣ የአደጋ ጊዜ ተጠሪዎቻችንን፣ አድራሻችንን እንዲሁም የስልክ ቁጥራችንን ከቀየርን ወይም (2) ሰነዱ ከጠፋብን አሊያም ከተበላሸብን ይሆናል።
የሕክምና መመሪያ ካርዱን እቤታችን ሆነን በጸሎት ልናስብበትና በጥንቃቄ ልንሞላው ይገባል። ሆኖም ካርዱ ላይ ከመፈረማችን በፊት ከሕግ ጋር የተያያዙ መመሪያዎችን በጥብቅ መከተል ይኖርብናል። ለአብነት ያህል፣ በምትፈርሙበት ጊዜ ሁለት ምሥክሮች ሊመለከቷችሁ እንደሚገባ ካርዱ የሚያዝዝ ከሆነ ስትፈርሙ እነዚህ ምሥክሮች ሊገኙ ይገባል። የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቾች አዲስ ካርድ ያልሞሉ አስፋፊዎች በሚሞሉበት ጊዜ እርዳታ ያስፈልጋቸው እንደሆነ ለማወቅ ሊጠይቋቸው ይችላሉ።
የሕክምና መመሪያ ካርዱን ከማጠፋችሁ በፊት ጥርት ብሎ በሚታይ መንገድ ፎቶ ኮፒ አድርጋችሁ ለአደጋ ጊዜ ተጠሪያችሁ፣ ለተጠባባቂ ተጠሪያችሁና ለሐኪማችሁ የምትሰጡት እንዲሁም ለራሳችሁ በፋይል ውስጥ የምታስቀምጡት ቅጂ አዘጋጁ። ለሌሎች የቤተሰባችሁ አባላትና ለጉባኤያችሁ ጸሐፊም የካርዱን ቅጂዎች መስጠት ትፈልጉ ይሆናል። እነዚህን ቅጂዎች ስታዘጋጁ የፎቶ ኮፒ ወረቀት በመጠቀም ካርዱን በወረቀቱ መሃል ላይ እንዲሰፍር አድርጉ፤ ፎቶ ኮፒ የምታደርጉት በወረቀቱ በአንደኛው ገጽ ላይ ብቻ መሆን አለበት። እናንተ ፎቶ ኮፒውን ሳይሆን ዋናውን ቅጂ መያዝ ይኖርባችኋል።
የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች የሚጠቀሙበት 3/99 የሚል ቀን የታተመበት የመታወቂያ ካርድ ላይ ለውጥ አልተደረገም። ወላጆች ልጃቸው የሚይዘው የመታወቂያ ካርድ በሚገባ መሞላቱንና መፈረሙን ማረጋገጥ እንዲሁም ልጁ አስፈላጊ በሚሆንባቸው ቦታዎች ሁሉ ይዞት እንዲሄድ ማድረግ አለባቸው።
ያልተጠመቁ አስፋፊዎች፣ የሕክምና መመሪያ ሰነዱን እንዲሁም የመታወቂያ ካርዱን መሠረት በማድረግ ለራሳቸውና ለልጆቻቸው የሕክምና መመሪያ ማዘጋጀት ይችላሉ። የጉባኤው ጸሐፊ በዓመቱ ውስጥ ለተጠመቁ አዳዲስ አስፋፊዎች ሁሉ የሕክምና መመሪያ ካርዱን ሊሰጣቸው ይገባል።