የቤተሰብ ፕሮግራም ይኑራችሁ—አብሮ ለማገልገል
1 ይሖዋ ልጆች ስሙን ሲያወድሱ መመልከት ያስደስተዋል። (መዝ. 148:12, 13) በኢየሱስ ዘመን ‘ልጆችና ጡት የሚጠቡ ሕፃናት’ ሳይቀሩ ይሖዋን አወድሰዋል። (ማቴ. 21:15, 16) ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ወላጆች፣ ልጆቻችሁ በክርስቲያናዊ አገልግሎት በመካፈል የይሖዋ ቀናተኛ አወዳሾች እንዲሆኑ እንዴት ልትረዷቸው ትችላላችሁ? ከላይ ባለው ርዕሰ ትምህርት ላይ ጐላ ተደርጎ እንደተጠቀሰው ቁም ነገሩ ያለው ምሳሌ በመሆናችሁ ላይ ነው። አንድ አባት “ልጆች ከምትነግሯቸው ነገር ይልቅ የምታደርጉትን ነገር ማድረግ ይቀናቸዋል!” በማለት የሁሉንም ወላጆች ስሜት ተናግሯል።
2 ፈሪሃ አምላክ ባላቸው ወላጆች ያደገች አንዲት እህት “ቅዳሜ ጠዋት ከእንቅልፋችን ስንነቃ አገልግሎት ስለ መሄዳችን ጠይቀን አናውቅም። አገልግሎት እንደምንሄድ እናውቅ ነበር” በማለት ሁኔታውን አስታውሳ ተናግራለች። በተመሳሳይ እናንተም፣ መላው ቤተሰባችሁ በየሳምንቱ አብሮ የማገልገል ልማድ እንዲያዳብር በማድረግ ልጆቻችሁ የስብከቱን ሥራ አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ ልታደርጉ ትችላላችሁ። ይህም ልጆቻችሁ እናንተን በማየት እንዲማሩ ብቻ ሳይሆን ያላቸውን አመለካከት፣ ጠባይና ችሎታ እንድታስተውሉ ይረዳችኋል።
3 ደረጃ በደረጃ ሥልጠና መስጠት:- ልጆች በአገልግሎት እንዲደሰቱ ከተፈለገ ውጤታማ ተሳትፎ ማድረግ በሚያስችላቸው መንገድ አስቀድሞ መዘጋጀት ያስፈልጋቸዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው እህት እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “በስብከት ሥራቸው ከወላጆቻችን ጋር የምንሄደው እንዲሁ እነሱን ለመከተል ብቻ አልነበረም። ምንም እንኳ የምናደርገው ነገር የበር ደወል በመደወልና የስብሰባ መጋበዣ ወረቀት በመስጠት ብቻ የተወሰነ ቢሆንም አንድ ዓይነት ተሳትፎ ማድረግ እንዳለብን እናውቅ ነበር። ቅዳሜና እሁድ ወደ አገልግሎት ከመውጣታችን በፊት በጥንቃቄ ስለምንዘጋጅ ምን መናገር እንዳለብን እናውቅ ነበር።” እናንተም በቤተሰብ ጥናታችሁ ወቅት ወይም በሌላ ጊዜ በየሳምንቱ ጥቂት ደቂቃዎችን ወስዳችሁ ልጆቻችሁን ለአገልግሎት በማዘጋጀት ይህን ዓይነቱን ሥልጠና መስጠት ትችላላችሁ።
4 በቤተሰብ አብሮ ማገልገል በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ እውነትን ለመቅረጽ ተጨማሪ አጋጣሚ ይከፍትላችኋል። አንድ ክርስቲያን አባት ከሚኖርበት መንደር ራቅ ብለው በሸለቆ ውስጥ ላሉ መንደርተኞች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትራክቶችን ለማሰራጨት ደርሶ መልስ 20 ኪሎ ሜትር የሚሆን መንገድ ሲጓዝ ሴት ልጁንም ይዟት ይሄድ ነበር። ይህች ልጅ ሁኔታውን በማስታወስ “አባቴ እውነትን በልቤ ውስጥ የተከለው ወደዚያ ሥፍራ በምናደርገው ጉዞ ላይ ነበር” ስትል በአድናቆት ተናግራለች። (ዘዳ. 6:7) አብሮ ማገልገልን የሳምንታዊው የቤተሰብ ፕሮግራማችሁ ክፍል በማድረግ እናንተም ተመሳሳይ በረከት ማግኘት ትችላላችሁ።