የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት እንዲያደርጉ መርዳት
ክፍል 11፦ ጥናቶቻችን ተመላልሶ መጠየቅ እንዲያደርጉ መርዳት
1 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ በስብከቱ ሥራ ላይ መሳተፍ ሲጀምር ለምሥራቹ ፍላጎት የሚያሳዩ ሰዎችን ማግኘቱ አይቀርም። ታዲያ ይህ አዲስ አስፋፊ ውጤታማ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግና ያገኛቸውን ሰዎች ፍላጎት ማሳደግ እንዲችል እንዴት ልንረዳው እንችላለን?
2 ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ዝግጅት መደረግ ያለበት በመጀመሪያው ውይይት ወቅት ነው። ጥናትህ ያነጋገራቸውን ሰዎች የመርዳት ልባዊ ፍላጎት እንዲያድርበት አበረታታው። (ፊልጵ. 2:4) ተማሪው የሚያነጋግራቸውን ሰዎች ሐሳባቸውን እንዲገልጹ መጋበዝ፣ የሚሰጡትን ሐሳብ በጥሞና ማዳመጥና የሚያሳስባቸውን ጉዳይ መረዳት የሚችለው እንዴት እንደሆነ ቀስ በቀስ አሠልጥነው። ፍላጎት ያሳየ ሰው ሲያጋጥምህ አዲሱ አስፋፊ በውይይቱ ውስጥ የተነሱትን ጠቃሚ ሐሳቦች በጽሑፍ እንዲያሰፍር አድርግ። ይህን መረጃ ለቀጣዩ ውይይት እቅድ ለማውጣት እንዲጠቀምበት እርዳው።
3 ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ መዘጋጀት:- የመጀመሪያውን ውይይት ከከለሳችሁ በኋላ መንግሥቱን በሚመለከት ሰውየውን ሊማርኩ የሚችሉ ሐሳቦችን መምረጥ የሚችልበትን መንገድ ለጥናትህ አሳየው። (1 ቆሮ. 9:19-23) ከማስጠኛ ጽሑፍ ላይ በአንድ አንቀጽና በዚያ ውስጥ በሚገኝ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ የተመሠረተ አጠር ያለ ውይይት እንዴት ማድረግ እንደሚችል አብራችሁ ተዘጋጁ። በተጨማሪም ለቀጣዩ ውይይት መሠረት መጣል እንድትችሉ በውይይቱ መደምደሚያ ላይ የምታነሷቸውን ጥያቄዎች አዘጋጁ። በምታደርጓቸው ቀጣይ ተመላልሶዎች ሰውየው ስለ አምላክ ቃል ያለውን እውቀት ደረጃ በደረጃ እንዲያሳድግ እንዴት መርዳት እንደሚችል ለአስፋፊው አሳየው።
4 በተጨማሪም ጥናትህ በተመላልሶ መጠየቅ ጊዜ ሊጠቀምበት የሚችል ቀለል ያለ መግቢያ እንዲዘጋጅ መርዳት ጠቃሚ ነው። ከቤቱ ባለቤት ጋር ሰላምታ ከተለዋወጠ በኋላ እንደሚከተለው ለማለት ይችላል:- “ባለፈው ጊዜ ባደረግነው ውይይት በጣም ተደስቻለሁ፤ አሁን ተመልሼ የመጣሁት ስለ [ቀደም ሲል የተወያያችሁበትን ርዕሰ ጉዳይ ጥቀስ] ተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳቦችን ላካፍልዎት ነው።” የቤቱን በር ሌላ ሰው ቢከፍት ምን ለማለት እንደሚችል ለአዲሱ አስፋፊ ማሳየት ይኖርብህ ይሆናል።
5 ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ረገድ ትጉዎች ሁኑ:- ጥናትህ ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ሁሉ ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ረገድ ጥሩ ምሳሌ እንዲሆን አበረታታው። ሰዎችን ቤታቸው ማግኘት ሳይሰለቹ ተመልሶ መሄድ ይጠይቃል። በድጋሚ ለመገናኘት እንዴት ቀጠሮ መያዝ እንደሚችልና ቃል በገባው መሠረት ተመልሶ የመሄዱን አስፈላጊነት እንዲገነዘብ እርዳው። (ማቴ. 5:37) በግ መሰል የሆኑ ሰዎችን ለመፈለግና ፍላጎታቸውን ለማሳደግ ርኅሩኅ፣ አሳቢና አክብሮት ያለው እንዲሆን አዲሱን አስፋፊ አሠልጥነው።—ቲቶ 3:2