ልጆችህ በአገልግሎት እድገት እንዲያደርጉ እርዳቸው
1 ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን ከትንሽነታቸው ጀምሮ ለአገልግሎት የማሠልጠን ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። ይህን ማድረግ የሚችሉባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። አንዳንድ ልጆች ማንበብ ከመጀመራቸው በፊት እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቃላቸው መናገር ይችላሉ። ይህ ደግሞ በአድማጮች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል። ልጆቹ እያደጉ በሄዱ መጠን በአገልግሎት ላይ ከዚህ የበለጠ ነገር ማድረግ ይችላሉ። እናንት ወላጆች፣ ልጆቻችሁ በምሥክርነቱ ሥራ እንዲካፈሉ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው? ቀጥለው የቀረቡት ሐሳቦች ተጨማሪ እርዳታ ያበረክቱላችሁ ይሆናል።
2 ሰላምታ ከተለዋወጣችሁ በኋላ እንደሚከተለው ማለት ትችል ይሆናል:-
◼ “ጤና ይስጥልኝ፤ ልጄ [ስሟን ጥቀስ] በአካባቢያችን የሚገኙ ሰዎችን መርዳት የምትችል ጠቃሚ ዜጋ እንድትሆን እያሠለጠንኳት ነው። ለእርስዎም ጥቂት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳቦችን ልታካፍልዎ ትፈልጋለች።” እሷም በመቀጠል እንዲህ ልትል ትችላለች:- “ሰዎችን ለመርዳት ከምፈልግባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ ስለመጪው ጊዜ የያዘውን ተስፋ እንዲያውቁ ማድረግ ነው። [ልጅቷ ራእይ 21:4ን ታነባለች ወይም በቃሏ ትጠቅሳለች።] እነዚህ መጽሔቶች የአምላክ መንግሥት የምታስገኝልንን ጥቅሞች ይገልጻሉ። ቢያነቧቸው እንደሚደሰቱ እርግጠኛ ነኝ።”
3 ልጆች ቀለል ያሉ አቀራረቦችን በተደጋጋሚ መጠቀማቸው የመንግሥቱን መልእክት ለመመሥከር ባላቸው ችሎታ ላይ የመተማመን መንፈስ እንዲያድርባቸው ያደርጋል። ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲሁም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲናገሩ ትኩረት ሰጥቶ ማሠልጠን በየትኛውም ሁኔታ ሥር ለመመሥከር ያስችላቸዋል። አስቀድሞ ጥሩ ዝግጅት ማድረግና ከልብ ማመስገን ልጆች ያመኑበትን ነገር ለሌሎች እንዲናገሩ ያበረታታቸዋል።
4 እንዲህ ዓይነቱ ማበረታቻ የተሰጣቸው በርካታ ልጆች ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ሆነው የማገልገል ብቃት አግኝተዋል። ልጆቻችን በክርስቲያናዊው አገልግሎት እድገት ሲያደርጉ መመልከት ምንኛ ያስደስታል!—መዝ. 148:12, 13