የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ ውድ መብት ነው
1 በየዕለቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ የምድር ነዋሪዎች ይሖዋ በደግነት ከሚያቀርባቸው ሕይወትን ለማቆየት አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች ይጠቀማሉ። (ማቴ. 5:45) የአምላክን መንግሥት ምሥራች የመስበኩን ልዩ መብት በመጠቀም ለፈጣሪያቸው ያላቸውን አመስጋኝነት የሚገልጹት ግን በጣም ጥቂት ናቸው። (ማቴ. 24:14) ግሩም ለሆነው ለዚህ መብት ያለህ አድናቆት ምን ያህል ከፍተኛ ነው?
2 የመንግሥቱ ስብከት አምላክን ከማስከበሩም ባሻገር ሁከት በነገሠበት በዚህ ዘመን ለተጨነቁ ሰዎች ተስፋና ሰላም ያስገኝላቸዋል። (ዕብ. 13:15) ይህን መልእክት የሚቀበሉ ሰዎች የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ይኖራቸዋል። (ዮሐ. 17:3) እንዲህ ያሉትን ጥቅሞች ማስገኘት የሚችል ሰብዓዊ ሥራ አሊያም ልዩ ሙያ የትኛው ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎቱን የፈጸመበት መንገድ ለሥራው አድናቆት እንደነበረው ያሳያል። አገልግሎቱን እንደ ውድ ሀብት ይመለከተው ነበር።—ሥራ 20:20, 21, 24፤ 2 ቆሮ. 4:1, 7
3 ውድ ለሆነው መብታችን አድናቆት እናሳይ:- ለስብከት መብታችን አድናቆት እንዳለን የምናሳይበት አንዱ መንገድ ለአገልግሎታችን ጥራት ትኩረት በመስጠት ነው። የአድማጮቻችንን ልብ የሚነካ መግቢያ ለመዘጋጀት በቂ ጊዜ ዋጅተናል? የጥቅስ አጠቃቀም ዘዴያችንን ብሎም ሰዎችን በምክንያት የማስረዳት ችሎታችንን ማሳደግ እንችል ይሆን? የአገልግሎት ክልላችንን አጣርተን እንሸፍናለን? የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመርም ሆነ መምራት እንችላለን? እንደ ጥንቶቹና ዛሬ እንዳሉት ታማኝ ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም ለዚህ ሥራ ተገቢ አመለካከት ያለን ሲሆን መብታችንንም ከፍ አድርገን እናያለን።—ማቴ. 25:14-23
4 ከዕድሜ መግፋት፣ ከሕመም አሊያም ከሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ጋር እየታገልን ቢሆንም እንኳ በአገልግሎት ላይ በቅንዓት ለመካፈል የምናደርገው ጥረት ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው ማወቃችን ያጽናናል። ይሖዋ እርሱን ለማገልገል የምናደርገውን እንዲህ ያለውን ጥረት ሌላው ቀርቶ ሰዎች ከቁብ የማይቆጥሩትን እንኳ ትልቅ ዋጋ እንደሚሰጠው የአምላክ ቃል ያረጋግጥልናል።—ሉቃስ 21:1-4
5 የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ከፍተኛ የእርካታ ስሜት ያስገኝልናል። የ92 ዓመት አረጋዊት እህት እንዲህ ብለዋል:- “ራሴን ለአምላክ በመወሰን ከ80 ለሚበልጡ ዓመታት ያቀረብኩትን አገልግሎት መለስ ብዬ መመልከት መቻሌ ትልቅ መብት ነው! አንድም የምቆጭበት ነገር የለም! ያሳለፍኩትን ሕይወት መድገም ብችል ኖሮ በዚያው መልክ እኖር ነበር። ምክንያቱም ‘የአምላክ ምሕረት ከሕይወት ይሻላልና’።” (መዝ. 63:3) እኛም ብንሆን ከአምላክ የተሰጠንን ግሩም መብት ማለትም የመንግሥቱን ስብከት ሥራችንን ከፍ አድርገን እንመልከት።