የስብሰባ መጋበዣ ወረቀቶችን ትጠቀማላችሁ?
አንድ ቀን አንድ የ11 ዓመት ልጅ ሲኦልን አስመልክቶ የሚቀርብ የሕዝብ ንግግር እንዳለ የሚያስተዋውቅ መጋበዣ ወረቀት አገኘ። ይህ ልጅ ከጊዜ በኋላ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ሁልጊዜ መጥፎ ነገር ስለማደርግና ስሞት ሲኦል ገብቼ እቃጠላለሁ የሚለው ሐሳብ በጣም ያስጨንቀኝ ስለነበር ይህ ርዕስ ቀልቤን ሳበው።” ይህ ልጅ ንግግሩን በቦታው ተገኝቶ ከማዳመጡም በላይ በርከት ላሉ ጊዜያት መጽሐፍ ቅዱስ ሲማር ቆይቶ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ተጠመቀ። ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል ሆኖ ለብዙ ዓመታት ያገለገለው የወንድም ካርል ክላይን ክርስቲያናዊ ሕይወት የጀመረው በዚህ መልኩ ነበር። ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው በአንዲት የመጋበዣ ወረቀት አማካኝነት ነው።
የስብሰባ መጋበዣ ወረቀቶች ዛሬም ቢሆን ምሥክርነቱን ለመስጠት የሚያስችሉ ውጤታማ መሣሪያዎች ናቸው። ብዙ አስፋፊዎች መጋበዣ ወረቀት መስጠት ራሳቸውን ለማስተዋወቅም ሆነ ውይይት ለመጀመር ቀላል ዘዴ ሆኖ አግኝተውታል። ወላጆች ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ ልጆቻቸው የስብሰባ መጋበዣ ወረቀት እንዲሰጡ በማድረግ አገልግሎት ላይ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ ይችላሉ። በደብዳቤ የሚመሠክሩ አስፋፊዎች መጋበዣ ወረቀት አያይዘው በመላክ ስብሰባዎችን ማስተዋወቅ ይችላሉ። ደግሞም የስብሰባ መጋበዣ ወረቀት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንና ፍላጎት ያሳዩ ሌሎች ሰዎች ወደ ስብሰባዎቻችን እንዲመጡ መጋበዝ የምንችልበት ጥሩ መንገድ ነው።
አገልግሎት ላይ በስብሰባ መጋበዣ ወረቀቶች በሚገባ ትጠቀማለህ?