“ክርስቶስን ተከተሉ!” የተባለውን የአውራጃ ስብሰባ በዓለም ዙሪያ ለማስተዋወቅ የሚደረግ ጥረት በዚህ ዓመትም አስፋፊዎች ልዩ የመጋበዣ ወረቀት ያሰራጫሉ
1 ባለፈው ዓመት “መዳናችን ቀርቧል!” የተባለውን የአውራጃ ስብሰባ ለማስተዋወቅ በዓለም ዙሪያ የተካሄደው ዘመቻ ፍላጎት ባላቸው ሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ልዩ የመጋበዣ ወረቀቱን ተቀብለው በስብሰባው ላይ የተገኙ ሰዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ሆነው ለመጀመሪያ ጊዜ በታላቅ መንፈሳዊ ድግስ ላይ ተገኝተዋል። (ኢሳ. 65:13) አንድነትና ፍቅር ካለው የወንድማማች ኅብረታችን ጋር አንድ ላይ በመሰብሰባቸው ተደስተዋል። (መዝ. 133:1) “ክርስቶስን ተከተሉ!” በተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ላይ በተቻለ መጠን በርካታ ሰዎች እንዲገኙ ለመርዳት በዚህ ዓመትም ልዩ የመጋበዣ ወረቀት በዓለም ዙሪያ እናሰራጫለን።
2 ባለፈው ዓመት የተገኙ ውጤቶች:- ከዓለም ዙሪያ የተሰበሰቡት ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት “መዳናችን ቀርቧል!” የተባለውን የአውራጃ ስብሰባ ለማስተዋወቅ በተደረገው ጥረት እጅግ በጣም አስደሳች ውጤቶች ተገኝተዋል። በብዙ አካባቢዎች በሰዎች ዘንድ ጥሩ ስም አትርፈናል። ለምሳሌ ያህል በአንድ ከተማ የሚታተም ጋዜጣ ዘመቻውን አስመልክቶ ባለ ስድስት አምድ ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። ጋዜጣው እንዲህ ብሏል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባው የሚደረግበት ቀን ከመድረሱ በፊት እያንዳንዱን ሰው ለማግኘት ሲሉ ለረጅም ሰዓታት በመሥራት፣ ሩቅ መንገዶችን በመጓዝና ንግግራቸውን አጭር በማድረግ በአካባቢያቸው ትጋት የተሞላበት ልዩ ጥረት አድርገዋል።” በሌላ ከተማ ደግሞ በተቀናጀ ሁኔታ ይሰራጭ የነበረው የመጋበዣ ወረቀት የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት በመሳቡ ሰፊ የዜና ሽፋን አግኝቷል። ቢያንስ ሦስት ጋዜጦች ስብሰባው ከመደረጉ በፊት ስላደረግነው እንቅስቃሴ በአድናቆት ዘግበዋል። አንድ የዜና ዘጋቢ በአንድ ጋዜጣ የእሁድ ዕለት እትም ላይ ከሁለት ገጽ በላይ የሚሸፍኑ ሰፋ ያሉ ርዕሶችን ጽፎ ነበር። ዘገባው ስለ እምነታችን፣ ስለ ወንድማማች ኅብረታችን፣ ስለ መጋበዣ ወረቀቱ ስርጭትና ስለ አውራጃ ስብሰባው ዝርዝር መግለጫ ያካተተ ነበር። አንዲት አስፋፊ የመጋበዣውን ወረቀት ከቤት ወደ ቤት በምታድልበት ወቅት የቤቱ ባለቤት አቋረጠቻትና “ስለዚህ ጉዳይ አሁን ጋዜጣ ላይ እያነበብኩ ነበር!” በማለት ነገረቻት። ሌላ ሴት ደግሞ “የመጣችሁት ጋዜጣ ላይ ስለ እናንተ እያነበብኩ እያለ ነው! ይህ የእኔ መጋበዣ ወረቀት ነው?” በማለት ጠይቃለች። አክላም “የይሖዋ ምሥክሮች የሚሠሩት ይህ ሥራ የሚያስመሰግናቸው ነው” ብላለች።
3 ፍላጎት ያላቸው በርካታ ግለሰቦች ስብሰባው ወደሚደረግበት ቦታ የመጡት የመጋበዣ ወረቀቱን ይዘው ነበር። አንዳንዶቹ በስብሰባው ላይ ለመገኘት በመኪና ከሩቅ ከተማ ተጉዘው የመጡ ናቸው። ሌሎችን ለመጋበዝ የምናደርገው ትጋት የታከለበት ጥረት የተሰብሳቢዎች ቁጥር እንዲጨምር አስተዋጽኦ ያበረክታል። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ አገር በአውራጃ ስብሰባ ላይ የተገኙት ተሰብሳቢዎች ቁጥር ቀደም ሲል ከነበረው ዓመት 27 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
4 ክልል የሚሸፈንበት መንገድ:- ስብሰባው የሚደረግበት ቀን ከመድረሱ ሦስት ሳምንት ቀደም ብላችሁ መጋበዣውን ማሰራጨት መጀመር ትችላላችሁ። ሙሉውን የጉባኤውን ክልል ለመሸፈን ከፍተኛ ጥረት መደረግ ይኖርበታል። ሰፊ ክልል ባላቸው ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ አስፋፊዎች ስብሰባው ሊጀምር አንድ ሳምንት ሲቀረው ቤታቸው ላልተገኙ ሰዎች መጋበዣውን በጥንቃቄ በራቸው ላይ ትተውላቸው መሄድ ይችላሉ። ጉባኤዎች የተላከላቸውን የመጋበዣ ወረቀት በሙሉ ለመጠቀም እንዲሁም በተቻለ መጠን በርካታ ክልሎችን ለመሸፈን ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። የሚተርፍ የመጋበዣ ወረቀት ካለ በጉባኤው ውስጥ ያሉት አቅኚዎች ወስደው እንዲያሰራጩት ማድረግ ይቻላል።
5 መጋበዣውን ስናሰራጭ ምን ማለት እንችላለን:- እንዲህ ልትል ትችላለህ:- “ሰዎች በቅርቡ በሚደረግ አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ይህን የመጋበዣ ወረቀት በዓለም ዙሪያ እያሰራጨን ነው። ይህ የእርስዎ የግል ቅጂ ነው። ተጨማሪ ማብራሪያዎችን በመጋበዣ ወረቀቱ ላይ ያገኛሉ።” አቀራረባችሁን አጭር ማድረጋችሁ በርካታ የመጋበዣ ወረቀት ማሰራጨት እንድትችሉ ይረዳችኋል። እርግጥ ነው፣ የቤቱ ባለቤት ጥያቄዎች ካሉት ጊዜ ወስዳችሁ ልታወያዩት ትችላላችሁ። የመወያየት ፍላጎት ያለው ሰው ካጋጠማችሁ ስሙን መዝግባችሁ በመያዝ በተቻለ ፍጥነት ተመልሳችሁ አነጋግሩት።
6 ክርስቶስን ለመከተል ጥረት ማድረጋችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! (ዮሐ. 3:36) መጪው የአውራጃ ስብሰባችን በስብሰባው ላይ የሚገኙት ሁሉ ይህን ማድረግ እንዲችሉ ይረዳቸዋል። “ክርስቶስን ተከተሉ!” የተሰኘውን የአውራጃ ስብሰባ ለማስተዋወቅ በሚደረገው ጥረት በዚህ ዓመትም ከፍተኛ ምሥክርነት እንደሚሰጥ ተስፋ እናደርጋለን። በመሆኑም በርካታ ሰዎች በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ በቅንዓት አገልግሉ። በዓለም ዙሪያ በሚደረገው በዚህ ዘመቻ ለመካፈል እያንዳንዳችሁ የምታደርጉትን ጥረት ይሖዋ አብዝቶ እንዲባርክላችሁ እንመኛለን።