ቀጥተኛ ግብዣ
1. ሰዎች በክልል ስብሰባ ላይ እንዲገኙ የመጋበዙ ዘመቻ የሚጀምረው መቼ ነው?
1 ለጓደኞቻችሁ ወይም ለቤተሰቦቻችሁ ብዙ ጉልበትና ወጪ የሚጠይቅ ልዩ የምግብ ግብዣ ለማድረግ ብታስቡ ግብዣው ላይ እንዲገኙ የምትጠሯቸው በደስታ ስሜት እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም። በተመሳሳይም በቅርቡ በምናካሂደው የክልል ስብሰባ ላይ የሚቀርበውን መንፈሳዊ ድግስ ለማዘጋጀት ብዙ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ይሖዋ፣ ስብሰባው ከመጀመሩ ከሦስት ሳምንት ቀደም ብለን ሰዎች በዚህ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ የመጋበዝ መብት ሰጥቶናል። ታዲያ ግብዣውን በደስታ ስሜት ማቅረብ እንድንችል ምን ይረዳናል?
2. በዘመቻው ላይ ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያነሳሳን ምንድን ነው?
2 ይሖዋ በክልል ስብሰባዎች አማካኝነት የሚሰጠን መመሪያ በግለሰብ ደረጃ ምን ያህል እንደሚጠቅመን የምናሰላስል ከሆነ በዘመቻው ላይ ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ እንነሳሳለን። (ኢሳ. 65:13, 14) በተጨማሪም በየዓመቱ የምናደርገው ይህ ዘመቻ ውጤት እንዳለው ማስታወስ ይኖርብናል። (“ውጤት ያስገኛል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ከምንጋብዛቸው ሰዎች መካከል ሁሉም ባይመጡም አንዳንዶቹ ስብሰባው ላይ ይገኛሉ። ግብዣውን ተቀብለው የሚመጡት ሰዎች ቁጥር ብዙም ይሁን ጥቂት የመጋበዣ ወረቀቱን ለማሰራጨት ከልብ ጥረት ማድረጋችን ለይሖዋ ክብር የሚያመጣ ከመሆኑም ሌላ የእሱን ለጋስነት ያሳያል።—መዝ. 145:3, 7፤ ራእይ 22:17
3. የመጋበዣ ወረቀቱን ማሰራጨት የሚቻለው እንዴት ነው?
3 የእያንዳንዱ ጉባኤ የሽማግሌዎች አካል፣ የመጋበዣ ወረቀቱን በጉባኤው ክልል ውስጥ ለብዙ ሰዎች ማዳረስ ስለሚቻልበት መንገድ ተነጋግሮ መወሰን አለበት፤ ይህም ቤታቸው ላልተገኙ ሰዎች የመጋበዣ ወረቀቱን ትቶ መሄድ ወይም የመጋበዣ ወረቀቱን በአደባባይ ምሥክርነት ማሰራጨት ያስፈልግ እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰንን ይጨምራል። ቅዳሜና እሁድ፣ ሁኔታው አመቺ እንደሆነ ከተሰማን መጽሔቶችንም ማበርከት እንችላለን። በዚህ ሥራ በደስታ ስሜት የምንካፈልና ይሖዋ በሚያቀርበው መንፈሳዊ ድግስ ላይ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች እንዲገኙ የምንጋብዝ ከሆነ ዘመቻው ሲጠናቀቅ ከፍተኛ እርካታ እንደምናገኝ የታወቀ ነው!