የመታሰቢያው በዓል የመጋበዣ ወረቀት ሚያዝያ 2 መሰራጨት ይጀምራል
1. በዚህ ዓመት የመታሰቢያው በዓል የመጋበዣ ወረቀት መሰራጨት የሚጀምረው መቼ ነው? ይህ ዓመታዊ ዘመቻ መደረጉ ምን ጥቅም አለው?
1 በዓመቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል የመጋበዣ ወረቀት ከሚያዝያ 2 እስከ ሚያዝያ 17 እናሰራጫለን። ፍላጎት ያላቸው በርካታ ሰዎች ከዚህ ቀደም በየዓመቱ ላደረግናቸው ተመሳሳይ ዘመቻዎች በጎ ምላሽ ሰጥተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በመታሰቢያው በዓል ዕለት አንዲት ሴት ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ደውላ “አሁን ገና ቤት መግባቴ ነው፤ ከቤቴ በር ሥር የመጋበዣ ወረቀት አገኘሁ። በበዓሉ ላይ መገኘት ብፈልግም ስንት ሰዓት እንደሚጀምር እርግጠኛ አይደለሁም” በማለት ተናገረች። ያነጋገራት ወንድም መረጃውን ከመጋበዣው ወረቀት ላይ የቱ ጋ ማግኘት እንደምትችል ገለጸላት። በመጨረሻም ሴትየዋ “ዛሬ ማታ በዓላችሁ ላይ እገኛለሁ!” ብላለች።
2. የመጋበዣ ወረቀቱን ለማሰራጨት ምን ማለት እንችላለን?
2 የምናሰራጨው እንዴት ነው? ክልላችንን ለመሸፈን ያለን ጊዜ የተወሰነ በመሆኑ ውይይታችንን አጭር ማድረጋችን የተሻለ ነው። እንዲህ ማለት እንችላለን፦ “ጤና ይስጥልኝ። እሁድ ሚያዝያ 9, 2003 (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሚያዝያ 17, 2011) በዓለም ዙሪያ በሚከበር ዓመታዊ የመታሰቢያ በዓል ላይ ከቤተሰብዎ ጋር እንዲገኙ የመጋበዣ ወረቀት ብሰጥዎ ደስ ይለኛል። [የመጋበዣ ወረቀቱን ለቤቱ ባለቤት ስጠው።] ይህ ቀን ኢየሱስ የሞተበት ዕለት ነው። ከክርስቶስ ቤዛ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ የሚያብራራ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ንግግር ይቀርባል፤ ይህ የመጋበዣ ወረቀት ስብሰባው በአካባቢያችን የሚደረገው የትና በስንት ሰዓት እንደሆነ ይገልጻል።”
3. በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎችን መጋበዝ የምንችለው እንዴት ነው?
3 የጉባኤው ክልል ሰፊ ከሆነ ሽማግሌዎች ቤታቸው ላልተገኙ ሰዎች የመጋበዣ ወረቀቱን አላፊ አግዳሚው ሊያየው በማይችል ሁኔታ እንድታስቀምጡ ሊወስኑ ይችላሉ። ተመላልሶ መጠየቅ የምታደርጉላቸውን ሰዎች፣ ዘመዶቻችሁን፣ የሥራ ባልደረቦቻችሁን፣ አብረዋችሁ የሚማሩትንና የምታውቋቸውን ሌሎች ሰዎች መጋበዝ እንዳለባችሁ አትርሱ። ቅዳሜና እሁድ የመጋበዣ ወረቀቱን ስታሰራጩ ሁኔታው የሚፈቅድ ከሆነ መጽሔቶችንም አብራችሁ አበርክቱ። በሚያዝያ ወር ረዳት አቅኚ በመሆን በዚህ አስደሳች ዘመቻ ላይ የምታደርጉትን አስተዋጽኦ ከፍ ማድረግ ትችሉ ይሆን?
4. ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ የምንፈልገው ለምንድን ነው?
4 ግብዣው ላይ የሚገኙ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች እንዴት ያለ ግሩም ምሥክርነት ይጠብቃቸዋል! ይሖዋ ቤዛውን በማዘጋጀት ስላሳየው ታላቅ ፍቅር ይሰማሉ። (ዮሐ. 3:16) የአምላክ መንግሥት ለሰው ልጆች ስለሚያስገኘው ጥቅም ይማራሉ። (ኢሳ. 65:21-23) በተጨማሪም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የበለጠ ማወቅ ከፈለጉ አስተናጋጆችን እንዲጠይቁ ግብዣ ይቀርብላቸዋል። ቅን ልብ ያላቸው በርካታ ሰዎች ለዚህ ዘመቻ ምላሽ በመስጠት በመታሰቢያው በዓል ላይ አብረውን እንዲገኙ ጸሎታችን ነው!