የመታሰቢያው በዓል መጋበዣ በዓለም ዙሪያ ይሰራጫል!
1. ከመታሰቢያው በዓል በፊት በመላው ምድር ለማከናወን የታቀደው ልዩ ዘመቻ የትኛው ነው?
1 “ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት።” (ሉቃስ 22:19) የይሖዋ አገልጋዮች ኢየሱስ የሰጠውን ይህን መመሪያ በመታዘዝ ፍላጎት ካሳዩ ሰዎች ጋር ሆነው የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር መጋቢት 30, 2010 ይሰበሰባሉ። ለዚህ ዓላማ የተዘጋጀው ልዩ የመጋበዣ ወረቀት ከመጋቢት 13 እስከ መጋቢት 30 ባለው ጊዜ ውስጥ በመላው ምድር ይሰራጫል።
2. መጋበዣ ወረቀት ስናሰራጭ ምን ብለን መናገር እንችላለን?
2 መጋበዣውን ማሰራጨት የሚቻልበት መንገድ፦ የመጋበዣ ወረቀቱን ለቤቱ ባለቤት ሰጥተኸው ሽፋኑ ላይ ያለውን ሥዕል ካሳየኸው በኋላ እንዲህ ልትለው ትችላለህ፦ “መጋቢት 30 ምሽት ላይ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር ይሰበሰባሉ። ዛሬ ወደ እርስዎ የመጣሁት በመታሰቢያው በዓል ላይ ከነቤተሰብዎ እንዲገኙ ልጋብዝዎት ነው። ወዳጆችዎ ቢገኙም ደስ ይለናል።” በዓሉ የሚከበርበትን ሰዓትና ቦታ ልትነግረው ትችላለህ። እንደ ሁኔታው ሉቃስ 22:19ን አውጥተህ በዓሉን በተመለከተ መመሪያ የተሰጠበትን ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ልታነብለት ትችላለህ። ይሁን እንጂ መጋበዣ ወረቀቱን ለማሰራጨት ያለን ጊዜ የተወሰነ መሆኑን አትዘንጋ፤ በመሆኑም አቀራረባችን እጥር ምጥን ያለ ቢሆን ይመረጣል።
3. በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ እነማንን መጋበዝ እንችላለን?
3 የጉባኤያችሁ ክልል ሰፊ ከሆነ ሽማግሌዎች ቤታቸው ላልተገኙ ሰዎች በሄዳችሁበት የመጀመሪያ ዕለት የመጋበዣ ወረቀቱን በራቸው ላይ እንድታስቀምጡላቸው ሊወስኑ ይችላሉ። ከተቻለ ከመጋበዣው ወረቀቱ ጋር መጽሔቶችን ማበርከት ይቻላል። ተመላልሶ የምታደርግላቸውን ሰዎች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችህን፣ የሥራ ባልደረቦችህን፣ አብረውህ የሚማሩትን ልጆች፣ ዘመዶችህን፣ ጎረቤቶችህን እንዲሁም የምታውቃቸውን ሌሎች ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ መጋበዝ እንዳለብህ አትርሳ።
4. ይሖዋ ቤዛ በማዘጋጀት ላሳየን ፍቅር ያለን አድናቆት ምን እንድናደርግ ይገፋፋናል?
4 የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጅት አድርግ፦ የመታሰቢያው በዓል ሰሞን የአገልግሎት እንቅስቃሴያችንን ከፍ ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥርልናል። ረዳት አቅኚ ለመሆን ፕሮግራምህን ማስተካከል ትችል ይሆን? ጥሩ መንፈሳዊ እድገት በማድረግ ላይ የሚገኙ ልጆች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አሉህ? ከሆነ በዚህ ልዩ ዘመቻ ላይ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ሆነው ለማገልገል ብቃቱን ያሟሉ እንደሆነ ለማወቅ ሽማግሌዎችን አናግር። ይሖዋ ቤዛውን በማዘጋጀት ላሳየን ፍቅር ያለን አድናቆት በመታሰቢያው በዓል ላይ እንድንገኝ ብቻ ሳይሆን በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ከእኛ ጋር በበዓሉ ላይ እንዲገኙ እንድንጋብዝ ይገፋፋናል።—ዮሐ. 3:16