ጊዜያችሁን በጥበብ ተጠቀሙበት
1 ይሖዋን ለማስደሰት ያለን ፍላጎት በሕይወታችን ውስጥ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ትልቅ ቦታ እንድንሰጥ ይገፋፋናል። የአምላክ ቃል ‘ከሁሉ አስቀድመን መንግሥቱን እንድንሻ’ እንዲሁም ‘ከሁሉ የሚሻለውን ለይተን እንድናውቅ’ ያስተምረናል። (ማቴ. 6:33፤ ፊልጵ. 1:10) እምብዛም አስፈላጊ ላልሆኑ ነገሮች ሁለተኛ ቦታ በመስጠት መንግሥቱን ለማስቀደም ጊዜ መዋጀት የምንችለው እንዴት ነው?—ኤፌ. 5:15-17
2 ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን አስቀድሙ:- አስፈላጊ ባልሆኑ ነገሮች ጊዜያችሁ እንዳይባክን ፕሮግራም አውጡ። አንዳንዶች ወሩ እንደገባ የቀን መቁጠሪያቸው ላይ የተወሰኑ ቀናትን ለመስክ አገልግሎት በመመደብ ፕሮግራም ያወጣሉ። ከዚያም ያወጡትን ፕሮግራም ሌሎች ጉዳዮች እንዳያደናቅፉባቸው ይጠነቀቃሉ። ለስብሰባዎች፣ ለግል ጥናትና ለትላልቅ ስብሰባዎች የሚሆን ጊዜ ለመዋጀትም እንደዚህ ማድረግ እንችላለን። ብዙዎች እያንዳንዱን ቀን መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ለመጀመር ወይም ንባባቸውን ማታ ላይ ለማድረግ ፕሮግራም አውጥተዋል። ለእያንዳንዱ አስፈላጊ እንቅስቃሴ የተወሰነ ፕሮግራም አውጡ፤ እንዲሁም አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮች በፕሮግራማችሁ ውስጥ ጣልቃ እንዲገቡ አትፍቀዱ።—መክ. 3:1፤ 1 ቆሮ. 14:40
3 ዓለም የሚያቀርባቸውን ነገሮች በመጠቀም ረገድ ገደብ አብጁ:- በአንዳንድ አገሮች የተለያዩ ስፖርቶችን፣ ጨዋታዎችን፣ መዝናኛዎችን፣ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎችንና ሌሎች ነገሮችን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። ብዙዎች ቴሌቪዥን በመመልከት ወይም ኮምፒውተር በመጠቀም በጣም ረጅም ጊዜ ያሳልፋሉ። ሆኖም ዓለም በሚያቀርባቸው መዝናኛዎችና አዳዲስ መሣሪያዎች ከልክ በላይ መጠመድ የኋላ ኋላ ለሐዘን መዳረጉ አይቀርም። (1 ዮሐ. 2:15-17) በዚህም ምክንያት ቅዱሳን ጽሑፎች ይህንን ዓለም ሙሉ በሙሉ እንዳንጠቀምበት ይመክሩናል። (1 ቆሮ. 7:31) ይህንን ጥበብ ያዘለ ምክር በመከተል ለይሖዋ አምልኮ ቀዳሚውን ቦታ እንደምትሰጡ በአኗኗራችሁ ማሳየት ትችላላችሁ።—ማቴ. 6:19-21
4 ይህ ሥርዓት ሊጠፋ የቀረው ጊዜ በጣም አጭር ነው። ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በአንደኛ ደረጃ የሚያስቀምጡ ሰዎች ደስተኞች ይሆናሉ፤ እንዲሁም የአምላክን ሞገስ ያገኛሉ። (ምሳሌ 8:32-35፤ ያዕ. 1:25) እንግዲያው ይህን ውድ ዋጋ ያለውን ሀብታችንን ማለትም ጊዜያችንን በጥበብ እንጠቀምበት።