“በሙሉ ልብ” እንዲታዘዙ ሌሎችን መርዳት
1. ይሖዋ ከአምላኪዎቹ ምን ይፈልጋል?
1 ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማምለክ ታዛዥነት ወሳኝ ነው። (ዘዳ. 12:28፤ 1 ጴጥ. 1:14-16) በቅርቡ የአምላክ የቅጣት ፍርድ ‘እግዚአብሔርን በማያውቁትና ወንጌሉን በማይታዘዙት’ ላይ ይፈጸምባቸዋል። (2 ተሰ. 1:8) የአምላክ ቃል የያዘውን ትምህርት “በሙሉ ልብ” እንዲታዘዙ ሌሎችን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?—ሮሜ 6:17
2. ጠንካራ እምነት እንዲያዳብሩ ሌሎችን መርዳት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
2 እምነትንና ፍቅርን እንዲያዳብሩ በመርዳት:- በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ታዛዥነት ከእምነት ጋር ተያይዞ ተገልጿል። ሐዋርያው ጳውሎስ ታዛዥነትና እምነት ያላቸውን ዝምድና አስመልክቶ “በዘላለማዊ አምላክ ትእዛዝ . . . አምነው እንዲታዘዙ” በማለት ተናግሯል። (ሮሜ 16:25, 26) ዕብራውያን ምዕራፍ 11 ከይሖዋ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ የተጓዙ በርካታ የእምነት ምሳሌዎችን ይጠቅሳል። (ዕብ. 11:7, 8, 17) በሌላ በኩል ግን፣ አለመታዘዝ ከእምነት ማጣት ጋር የተያያዘ ነው። (ዮሐ. 3:36፤ ዕብ. 3:18, 19) ሌሎች ታዛዦች ለመሆን የሚያስችላቸውን እምነት እንዲያዳብሩ ለመርዳት እኛ ራሳችን የአምላክን ቃል በመጠቀም ረገድ ችሎታችንን ማዳበር ይኖርብናል።—2 ጢሞ. 2:15፤ ያዕ. 2:14, 17
3. (ሀ) ታዛዥነት ከፍቅር ጋር ተያይዞ የተገለጸው እንዴት ነው? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳድጉ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?
3 ታዛዥነት ለአምላክ ካለን ፍቅርም ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው። (ዘዳ. 5:10፤ 11:1, 22፤ 30:16) አንደኛ ዮሐንስ 5:3 ላይ “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና። ትእዛዛቱም ከባድ አይደሉም” ይላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳድጉ እንዴት መርዳት እንችላለን? በጥናቱ ወቅት ለይሖዋ ባሕርያት ያላቸውን አድናቆት ማሳደግ የምትችልባቸውን አጋጣሚዎች ለማግኘት ሞክር። ስለ አምላክ የሚሰማህን የራስህን ውስጣዊ ስሜት ግለጽለት። ተማሪው ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና ስለ መመሥረት እንዲያስብ እርዳው። እኛም ሆንን ሌሎች በሙሉ ልብ ታዛዦች እንድንሆን ከሁሉ በላይ የሚገፋፋን ለይሖዋ ያለን ፍቅር ነው።—ማቴ. 22:37
4. (ሀ) የእኛ ምሳሌ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) “ታዛዥ ልብ” ለማዳበር ምን ማድረግ ይኖርብናል?
4 ምሳሌ በመሆን:- ሌሎች ለምሥራቹ ታዛዦች እንዲሆኑ ለማበረታታት ውጤታማ የሆነው መንገድ እኛ ራሳችን ምሳሌ መሆን ነው። ይሁን እንጂ “ታዛዥ ልብ” ለማዳበር የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ ይጠይቅብናል። (1 ነገ. 3:9 NW፤ ምሳሌ 4:23) ይህስ ምን ማድረግን ይጨምራል? አዘውትራችሁ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና በጉባኤ ስብሰባዎች በመገኘት ልባችሁን መንፈሳዊ ምግብ መግቡት። (መዝ. 1:1, 2፤ ዕብ. 10:24, 25) ልባቸውን በእውነተኛው አምልኮ አንድ ካደረጉ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መሥርቱ። (ምሳሌ 13:20) በክልላችሁ ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች ለመርዳት ልባዊ ፍላጎት ኖሯችሁ ዘወትር በመስክ አገልግሎት ተካፈሉ። ጥሩ ልብ ለማዳበር እንዲረዳችሁ ይሖዋን በጸሎት ጠይቁት። (መዝ. 86:11) ልባችሁን ሊያበላሽ ከሚችል ሥነ ምግባር የጎደለው ወይም ዓመጽ የሚንጸባረቅበት መዝናኛ ራቁ። ወደ አምላክ የሚያቀርቧችሁንና ከእሱ ጋር ያላችሁን ዝምድና የሚያጠናክሩላችሁን ነገሮች አድርጉ።—ያዕ. 4:7, 8
5. ታዛዦች የሚባረኩት እንዴት ነው?
5 ይሖዋ የጥንት ሕዝቦቹ ትእዛዙን ከሰሙ በረከት እንደሚያገኙ ዋስትና ሰጥቷቸው ነበር። (ዘዳ. 28:1, 2) ዛሬም በተመሳሳይ “እግዚአብሔር ለሚታዘዙት” የተትረፈረፈ በረከት ይሰጣቸዋል። (ሥራ 5:32) በምናስተምረው ትምህርትም ሆነ ራሳችን ምሳሌ በመሆን ሌሎች በሙሉ ልባቸው እንዲታዘዙ እንርዳ።