“ታዛዥ ልብ” አለህን?
ሰሎሞን የጥንቱ እስራኤል ንጉሥ እንዲሆን በተሾመ ጊዜ ብቁ አይደለሁም የሚል ስሜት ተሰምቶት ነበር። በዚህም የተነሳ ጥበብና እውቀት እንዲሰጠው አምላክን ለመነ። (2 ዜና መዋዕል 1:10) በተጨማሪም ሰሎሞን “በሕዝብህ ላይ መፍረድ ይችል ዘንድ፣ . . . ለባሪያህ አስተዋይ [“ታዛዥ፣” NW] ልቡና ስጠው” በማለት ጸልዮአል። (1 ነገሥት 3:9) ሰሎሞን ‘ታዛዥ ልብ’ ካለው መለኮታዊ ሕጎችንና መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይከተላል፤ የይሖዋንም በረከት ያገኛል።
ታዛዥ ልብ ሸክም ሳይሆን የደስታ ምንጭ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:3) በእርግጥም አምላክን መታዘዝ ይገባናል። ይሖዋ ታላቅ ፈጣሪያችን ነው። ምድርና በእርሷ ላይ ያለው ነገር ሁሉ ሌላው ቀርቶ ብሩና ወርቁ እንኳን ሳይቀር የእርሱ ንብረት ነው። ስለዚህ ጥሪታችንን ለእርሱ ያለንን ፍቅር ለመግለጽ እንድንጠቀምበት ቢፈቅድልንም እንኳ የእሱ ያልሆነ ምንም ዓይነት ቁሳዊ ነገር ልንሰጠው አንችልም። (1 ዜና መዋዕል 29:14) ይሖዋ እንድንወደውና ፈቃዱን እያደረግን በትሕትና ከእርሱ ጋር እንድንጓዝ ይጠብቅብናል።—ሚክያስ 6:8
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሕጉ መካከል ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው እንደሆነ በተጠየቀ ጊዜ “ጌታ [“ይሖዋ፣” NW] አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት” በማለት መልሷል። (ማቴዎስ 22:36-38) ይህን ፍቅር ማሳየት የምንችልበት አንደኛው መንገድ አምላክን በመታዘዝ ነው። ስለዚህ ሁላችንም ይሖዋ ታዛዥ ልብ እንዲሰጠን መጸለይ ይኖርብናል።
ታዛዥ ልብ ነበራቸው
መጽሐፍ ቅዱስ ታዛዥ ልብ የነበራቸውን ብዙ ሰዎች ምሳሌ ይጠቅስልናል። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ ሕይወትን ከጥፋት ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችል ግዙፍ መርከብ እንዲሠራ ኖኅን አዝዞት ነበር። ይህ 40 ወይም 50 ዓመት ገደማ የሚፈጅ ትልቅ ሥራ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ያሉ ዘመናዊ መሣሪያዎችና ሌሎች ለግንባታ ሥራ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ ቢውሉ እንኳ እንዲህ ያለ ሊንሳፈፍ የሚችል ግዙፍ አካል መገንባት ከፍተኛ የምህንድስና ሙያ የሚጠይቅ ከባድ ሥራ ይሆን ነበር። ከዚህም በላይ ኖኅ ለሚያላግጡበትና ለሚያፌዙበት ሰዎች ማስጠንቀቂያ ማሰማት ነበረበት። ይሁን እንጂ ትናንሽ በሆኑ ነገሮች እንኳን ሳይቀር ታዛዥ ነበር! መጽሐፍ ቅዱስ “እንዲሁ አደረገ” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 6:9, 22፤ 2 ጴጥሮስ 2:5) ኖኅ ለብዙ ዓመታት በታማኝነት ታዛዥ በመሆን ለይሖዋ ያለውን ፍቅር አሳይቷል። ለእኛ ለሁላችንም እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!
ከዚህም በተጨማሪ የዕብራውያን አባት የሆነውን አብርሃምን እንደ ምሳሌ አድርገን እንውሰድ። አምላክ የበለጸገችውን የከለዳውያን ከተማ ኡርን ለቅቆ ወደማያውቀው አገር እንዲሄድ ነገረው። አብርሃም ያለ ምንም ማንገራገር ትእዛዙን ተቀበለ። (ዕብራውያን 11:8) በቀረው የሕይወት ዘመኑ እሱና ቤተሰቡ በድንኳን ኖሩ። በሄደበት አገር ለብዙ ዓመታት እንግዳ ሆኖ ከኖረ በኋላ ይሖዋ እርሱንና ታዛዥ የነበረችውን ሚስቱን ሣራን ይስሐቅ የተባለ ወንድ ልጅ በመስጠት ባረካቸው። በ100 ዓመት ዕድሜ ላይ የነበረው አብርሃም በእርጅና ዘመኑ የወለደውን ይህን ልጅ ምን ያህል ይወደው እንደነበር መገመት አያዳግትም! ከጥቂት ዓመታት በኋላ ይሖዋ ይስሐቅን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርበው ለአብርሃም ጥያቄ አቀረበለት። (ዘፍጥረት 22:1, 2) አብርሃም ይህን ማድረጉ ቀርቶ ማሰቡ ብቻ እንኳ ዘግንኖት መሆን አለበት። የሆነ ሆኖ ለይሖዋ የነበረው ፍቅርና ተስፋ የተሰጠው ዘር በይስሐቅ በኩል እንደሚመጣና ቢሞት እንኳ አምላክ ከሙታን ሊያስነሳው እንደሚችል የነበረው እምነት ይሖዋን እንዲታዘዝ ገፋፍቶታል። (ዕብራውያን 11:17-19) ይሁን እንጂ አብርሃም ልጁን ሊሠዋው ሲል ይሖዋ አስቆመውና “አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደ ሆንህ አሁን አውቄአለሁ” በማለት ተናገረው። (ዘፍጥረት 22:12) ፈሪሃ አምላክ የነበረው አብርሃም ታዛዥ በመሆኑ ምክንያት “የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ።”—ያዕቆብ 2:23
ታዛዥ በመሆን በኩል ከሁሉ የሚበልጠው ምሳሌያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት በነበረው ሕልውና በሰማይ አባቱን በታዛዥነት ማገልገል ያስደስተው ነበር። (ምሳሌ 8:22-31) ሰው በነበረበትም ጊዜ ኢየሱስ በሁሉ ነገር ይሖዋን ታዟል፤ ፈቃዱን ማድረግ ዘወትር ያስደስተው ነበር። (መዝሙር 40:8፤ ዕብራውያን 10:9) በዚህም የተነሳ ኢየሱስ በትክክል እንዲህ ለማለት ችሏል:- “አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገር ዘንድ እንጂ ከራሴ አንዳች እንዳላደርግ በዚያን ጊዜ ታውቃላችሁ። የላከኝም ከእኔ ጋር ነው፤ እኔ ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁና አብ ብቻዬን አይተወኝም።” (ዮሐንስ 8:28, 29) በመጨረሻም ኢየሱስ የይሖዋን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥና ታዛዥ የሰው ልጆችን ለመቤዠት ሲል እጅግ በሚያዋርድና በሚያሠቃይ መንገድ ለመሞት ሕይወቱን በፈቃደኝነት አቀረበ። “በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፣ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።” (ፊልጵስዩስ 2:8) ታዛዥ ልብ በማሳየት በኩል እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!
በከፊል መታዘዝ በቂ አይደለም
አምላክን እንታዘዛለን ያሉ ሁሉ በትክክል ይታዘዙታል ማለት አይቻልም። የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረውን ሳኦልን እንውሰድ። አምላክ ክፉ የነበሩትን አማሌቃውያንን ጠራርጎ እንዲያጠፋ መመሪያ ሰጥቶት ነበር። (1 ሳሙኤል 15:1-3) ምንም እንኳ ሳኦል በብሔር ደረጃ ያጠፋቸው ቢሆንም ንጉሣቸውን እንዲሁም በጎቻቸውንና ከብቶቻቸውን ሳያጠፋ በሕይወት ይዟቸው ተመለሰ። ሳሙኤል “ለምን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህም?” ሲል ጠየቀው። ሳኦልም መልሶ “የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቻለሁ፣ . . . ሕዝቡ [የእስራኤል ሕዝብ] ግን . . . ለእግዚአብሔር . . . ይሠዉ ዘንድ ከእርሙ የተመረጡትን በጎችንና በሬዎችን ከምርኮው ወሰዱ አለው።” ሳሙኤል ሙሉ በሙሉ የመታዘዝን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ በመግለጽ እንዲህ በማለት መለሰለት:- “በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፣ መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል። ዓመፀኝነት እንደ ምዋርተኛ ኃጢአት፣ እልከኝነትም ጣዖትንና ተራፊምን እንደ ማምለክ ነው፤ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና እግዚአብሔር ንጉሥ እንዳትሆን ናቀህ።” (1 ሳሙኤል 15:17-23) ሳኦል ታዛዥ ልብ ስላልነበረው ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበታል!
ታዛዥ ልብ እንዲሰጠው አምላክን በጸሎት ጠይቆ የነበረው ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን እንኳን ለይሖዋ ታዛዥ ሆኖ አልቀጠለም። ከመለኮታዊ ፈቃድ ጋር በመቃረን በአምላክ ላይ ኃጢአት እንዲሠራ ያደረጉትን የባዕድ አገር ሴቶች አገባ። (ነህምያ 13:23, 26) ሰሎሞን ታዛዥ ልብ ይዞ ስላልዘለቀ የነበረውን መለኮታዊ ሞገስ አጣ። ይህ ለእኛ እንዴት ያለ ማስጠንቀቂያ ነው!
እንዲህ ሲባል ግን ይሖዋ ከሰብዓዊ አገልጋዮቹ ፍጽምናን ይጠብቃል ማለት አይደለም። ‘አፈር መሆናችንን ያስባል።’ (መዝሙር 103:14) ሁላችንም አልፎ አልፎ ስህተት መሥራታችን የማይቀር ነው፤ ሆኖም አምላክ በእርግጥ እርሱን ለማስደሰት ልባዊ ምኞት እንዳለንና እንደሌለን ማወቅ ይችላል። (2 ዜና መዋዕል 16:9) በሰብዓዊ አለፍጽምና ምክንያት ስህተት ብንፈጽምና ንስሐ ብንገባ ይሖዋ ‘በብዙ ይቅር እንደሚል’ በመተማመን በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት መሠረት ይቅርታ ልንጠይቅ እንችላለን። (ኢሳይያስ 55:7፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2) በመንፈሳዊ እንድናገግም እንዲሁም ጤናማ እምነትና ታዛዥ ልብ እንዲኖረን የአፍቃሪ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እርዳታ ሊያስፈልገን ይችላል።—ቲቶ 2:2፤ ያዕቆብ 5:13-15
ታዛዥነታችሁ ምን ያህል የተሟላ ነው?
የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን አብዛኞቻችን ታዛዥ ልብ እንዳለን ምንም አንጠራጠርም ይሆናል። ምናልባትም እንዲህ እንል ይሆናል:- በመንግሥቱ የስብከት ሥራ እየተካፈልኩ አይደል እንዴ? የገለልተኝነትን ጥያቄ የመሰሉ አንዳንድ ከበድ ያሉ ጉዳዮች በሚነሱበት ጊዜ የጸና አቋም እወስዳለሁ። በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ በሰጠው ማሳሰቢያ መሠረት አዘውትሬ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እገኛለሁ። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20፤ ዮሐንስ 17:16፤ ዕብራውያን 10:24, 25) አዎን፣ የይሖዋ ሕዝቦች በቡድን ደረጃ እንዲህ በመሰሉ ትላልቅ ጉዳዮች ልባዊ ታዛዥነት ያሳያሉ።
ይሁን እንጂ በዕለታዊ ጉዳዮች የምናሳየው ምግባር ምናልባትም ጥቃቅን በሚመስሉ ጉዳዮች ያለን አቋም እንዴት ነው? ኢየሱስ “ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው፣ ከሁሉ በሚያንስም የሚያምፅ በብዙ ደግሞ ዓመፀኛ ነው” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 16:10) ስለዚህ እያንዳንዳችን ራሳችንን እንዲህ ብለን ብንጠይቅ ጥሩ ይሆናል:- ሌሎች ሰዎች ፈጽሞ በማያዩአቸው ጥቃቅን በሚመስሉ ነገሮች ወይም ጉዳዮች ጭምር ታዛዥ ልብ እንዳለኝ አሳያለሁን?
መዝሙራዊው ሌሎች በማያዩት ቦታ ማለትም በቤቱ እንኳን ሳይቀር ‘በንጹሕ ልቦና ተመላልሷል።’ (መዝሙር 101:2) ቤትህ ሆነህ ቴሌቪዥን ከፍተህ ፊልም መመልከት ጀመርክ እንበል። ወዲያው ታዛዥነትህ ፈተና ላይ ሊወድቅ ይችላል። ፊልሙ የጾታ ብልግና ሊያሳይ ይችላል። በአሁኑ ጊዜ የሚተላለፉት ፊልሞች እንዲህ ያሉ ናቸው የሚል ሰበብ በመፍጠር ፊልሙን መመልከትህን ትቀጥላለህ? ወይስ ታዛዥ የሆነው ልብህ ‘ዝሙትና ርኵሰት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ’ የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትእዛዝ እንድትፈጽም ይገፋፋሃል? (ኤፌሶን 5:3-5) ታሪኩ የሚስብ ቢሆን እንኳ ቴሌቪዥኑን ታጠፋለህ? ወይም የሚተላለፈው ፕሮግራም ጠበኝነትን የሚያሳይ በሚሆንበት ጊዜ ጣቢያውን ትቀይራለህ? “እግዚአብሔር ጻድቅንና ኀጥእን ይመረምራል፤ ዓመፃን የወደዳት ግን ነፍሱን ጠልቶአል” በማለት መዝሙራዊው ዘምሯል።—መዝሙር 11:5
ታዛዥ ልብ በረከት ያስገኛል
አምላክን በእርግጥ ከልባችን የምንታዘዝ መሆናችንን ለይተን ለማወቅ ራሳችንን ጠቃሚ በሆነ መንገድ መመርመር የምንችልባቸው ብዙ የሕይወት ዘርፎች አሉ። ለይሖዋ ያለን ፍቅር እርሱን እንድናስደስትና በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሰፈራቸውን ሁሉ እንድንፈጽም ሊገፋፋን ይገባል። ታዛዥ ልብ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና መሥርተን እንድንኖር ይረዳናል። በእርግጥም ሙሉ በሙሉ ታዛዦች ከሆንን ‘የአፋችን ቃልና የልባችን አሳብ በይሖዋ ፊት ያማረ ይሆናል።’—መዝሙር 19:14
ይሖዋ ስለሚወደን ለራሳችን ጥቅም ሲል ታዛዥ እንድንሆን ያስተምረናል። እንዲሁም በሙሉ ልባችን በመለኮታዊ ትምህርት ላይ የምናተኩር ከሆነ ራሳችንን በእጅጉ እንጠቅማለን። (ኢሳይያስ 48:17, 18) እንግዲያው ሰማያዊው አባታችን በቃሉ፣ በመንፈሱና በድርጅቱ በኩል የሚሰጠንን እርዳታ በደስታ እንቀበል። በሚገባ እየተማርን በመሆኑ “መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ” የሚል ድምፅ ከበስተኋላችን የምንሰማ ያክል ነው። (ኢሳይያስ 30:21) ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በክርስቲያናዊ ጽሑፎችና በጉባኤ ስብሰባዎች በሚያስተምረን ጊዜ በትኩረት የምንከታተል፣ የተማርናቸውን በተግባር ላይ የምናውልና ‘በሁሉም ነገር የምንታዘዝ’ እንሁን።—2 ቆሮንቶስ 2:9
ታዛዥ ልብ ከፍተኛ ደስታና እጥፍ ድርብ በረከቶችን ያስገኛል። ይሖዋ አምላክን ደስ እያሰኘንና ልቡ በሐሴት እንዲሞላ እያደረግን እንዳለን ማወቃችን የአእምሮ ሰላም ያስገኝልናል። (ምሳሌ 27:11) ታዛዥ የሆነ ልብ ስህተት እንድንሠራ በምንፈተንበት ጊዜ ይጠብቀናል። እንግዲያው ሰማያዊ አባታችንን መታዘዝ ይኖርብናል፤ እንዲሁም “ለባሪያህ አስተዋይ [“ታዛዥ፣” NW] ልቡና ስጠው” ብለን መጸለይ ይገባናል።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
From the Self-Pronouncing Edition of the Holy Bible, containing the King James and the Revised versions