የመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ
ኢየሱስ “መታዘዝን ተማረ”
ኢየሱስ ቀድሞም ቢሆን ለይሖዋ ታዛዥ ነበር። (ዮሐ. 8:29) ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ “ከደረሰበት መከራ መታዘዝን ተማረ” የሚለው ለምንድን ነው?—ዕብ. 5:8
ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ በሰማይ ላይ አጋጥመውት የማያውቁ ሁኔታዎች አጋጥመውታል። ለምሳሌ ወላጆቹ ለአምላክ ያደሩ ቢሆኑም ፍጹማን አልነበሩም። (ሉቃስ 2:51) ክፉ በሆኑ የሃይማኖት መሪዎችና ፍርደ ገምድል በሆኑ ባለሥልጣናት እጅ ብዙ መከራ ደርሶበታል። (ማቴ. 26:59፤ ማር. 15:15) በተጨማሪም “ራሱን ዝቅ በማድረግ እስከ ሞት ድረስ” ያውም በሚያሠቃይ ሁኔታ እስከመሞት ድረስ “ታዛዥ ሆኗል።”—ፊልጵ. 2:8
ኢየሱስ እነዚህ ነገሮች ስላጋጠሙት በሰማይ ላይ ከነበረው በተለየ ሁኔታ መታዘዝን ተምሯል። በመሆኑም ሊራራልን የሚችል ፍጹም ንጉሥና ሊቀ ካህናት ሊሆን ችሏል። (ዕብ. 4:15፤ 5:9) ኢየሱስ ከደረሰበት መከራ መታዘዝን ከተማረ በኋላ በይሖዋ ዘንድ ይበልጥ ውድ ሆኗል፤ እንዲሁም ይሖዋ በተሻለ መንገድ ሊጠቀምበት ችሏል። እኛም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ታዛዥ ስንሆን በይሖዋ ዘንድ ይበልጥ ውድ እንሆናለን፤ እንዲሁም እሱ የሚሰጠንን ማንኛውንም ኃላፊነት በተሻለ መንገድ መወጣት እንችላለን።—ያዕ. 1:4