ለመስበክ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ፍጠሩ
1 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የተለያየ ሁኔታ ያላቸው ሰዎች ይገኛሉ። ያም ሆኖ ግን ሁላችንም ይሖዋን ለማወደስ ቁርጥ ውሳኔ በማድረጋችን አንድ ሆነናል። (መዝ. 79:13) ጤና ማጣት ወይም ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ምሥራቹን ለማወጅ የምናደርገውን ጥረት ቢገድቡብን ለመስበክ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር የምንችለው እንዴት ነው?
2 በዕለታዊ እንቅስቃሴያችን:- ኢየሱስ በየቀኑ ከሰዎች ጋር የሚገናኝበትን አጋጣሚ ምሥክርነት ለመስጠት ተጠቅሞበታል። በቀረጥ ማስከፈያ ኬላ በኩል በሚያልፍበት ጊዜ ማቴዎስን፣ በጉዞ ላይ እያለ ዘኬዎስን እንዲሁም በእረፍት ጊዜው አንዲት ሳምራዊት ሴትን አነጋግሯል። (ማቴ. 9:9፤ ሉቃስ 19:1-5፤ ዮሐ. 4:6-10) እኛም በተመሳሳይ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ተራውን ጭውውት ወደ ምሥክርነት መቀየር እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስንም ሆነ ትራክቶችን ወይም ብሮሹሮችን ሁልጊዜ መያዛችን ስለ ተስፋችን ለመናገር ዝግጁዎች እንድንሆን ያደርገናል።—1 ጴጥ. 3:15
3 እንደልብ መንቀሳቀስ አለመቻልህ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት እንዳትካፈል አድርጎሃል? ከሕክምና ባለሞያዎችም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር በምትገናኝበት ጊዜ ለመመሥከር የሚያስችሉህን አጋጣሚዎች ለመጠቀም ንቁ ሁን። (ሥራ 28:30, 31) ያለህበት ሁኔታ አብዛኛውን ጊዜ ከቤት እንዳትወጣ የሚያደርግህ ከሆነ በስልክ ወይም በደብዳቤ ለመመሥከር ለምን አትሞክርም? አንዲት እህት ለማያምኑ የቤተሰቧ አባላት አዘውትራ ደብዳቤ ትጽፋለች። ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱ የሚያበረታቱ ሐሳቦችንና ስትመሠክር ያገኘቻቸውን ተሞክሮዎች በደብዳቤዎቿ ውስጥ ታክላለች።
4 በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት:- ይሖዋን ለማወደስ ያለን ምኞት በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት የእውነትን ዘር ለመትከል አጋጣሚዎችን እንድንፈጥር ይገፋፋናል። አስፋፊ የሆነ አንድ የስምንት ዓመት ልጅ በክፍሉ ውስጥ ለሚገኙት ተማሪዎች ከንቁ! መጽሔት ስለ ጨረቃ ያነበበውን ሐሳብ ነገራቸው። አስተማሪዋ ሐሳቡን ከየት እንዳገኘው ከተረዳች በኋላ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን በየጊዜው መውሰድ ጀመረች። በሥራ ቦታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ሌሎች ሊያዩት በሚችሉት ቦታ ላይ ማስቀመጡ ብቻ ጥያቄ እንዲያነሱ ሊያደርጋቸው ይችላል፤ ይህ ደግሞ ለመመሥከር አጋጣሚ ይፈጥርልናል።
5 በዕለታዊ እንቅስቃሴህ ለሌሎች ለመስበክ አጋጣሚዎችን መፍጠር የምትችልበት መንገድ ይኖር ይሆን? የጤና እክል ያለባቸው አንዳንድ አስፋፊዎች ቤታቸው ደጃፍ ላይ ሆነው በመንገድ ለሚያልፉ ሰዎች በመስበክ ለመመሥከር የሚያስችላቸው ጥሩ አጋጣሚ ፈጥረዋል። ሁኔታዎቻችን በሚፈጥሩልን አጋጣሚዎች በሚገባ በመጠቀም በየቀኑ ‘የምስጋናን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ለማቅረብ’ እንትጋ።—ዕብ. 13:15