የቅርብ ረዳት
1 የማያምን ባል ያላትና ሥራ በጣም የሚበዛባት አና የተባለች አንዲት እህት አዘውትራ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት፣ በአገልግሎት ለመካፈልና የአምላክን ቃል ለማጥናት አስቸጋሪ ሆኖባት ነበር። ለይሖዋ ፍቅር የነበራት ብትሆንም ማገልገልና ጉባኤ መምጣት አቆመች። ደስ የሚለው ግን አሳቢ የሆኑ ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ አበረታቷት።
2 በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት የሚሰጠንን መንፈሳዊ እርዳታ መቀበላችን በይሖዋ ላይ እምነት እንዳለን ያሳያል። በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሽማግሌዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየውን ፍቅራዊ እንክብካቤ በመኮረጅ በመንፈሳዊ የደከሙትን ለማበረታታትና ተግባራዊ እርዳታ ለመስጠት አጋጣሚዎችን ይፈልጋሉ። (1 ተሰ. 5:14) አብዛኛውን ጊዜ የሚያስፈልገው በሚያጽናኑ ጥቅሶች ላይ ያተኮረ አሳቢነት የተሞላበት ማበረታቻ ብቻ ሊሆን ይችላል። በመንፈሳዊ የደከሙትን ቅድሚያ ወስዶ መርዳት የሽማግሌዎች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ክርስቲያኖች ኃላፊነት ነው። “ባግባቡ [“በወቅቱ፣” የ1980 ትርጉም ] የተነገረ ቃል” ምን ያህል ኃይል እንዳለው እያንዳንዳችን እንደተመለከትን ምንም ጥያቄ የለውም።—ምሳሌ 25:11፤ ኢሳ. 35:3, 4
3 ቅድሚያውን ውሰዱ:- እርዳታ ለሚያሻቸው ሰዎች አሳቢነት ለማሳየት ቅድሚያውን መውሰድ፣ ፍቅር ማሳየትና ልባዊ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ዮናታን ዳዊት በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ እንዳለ ሲረዳ “ዳዊት ወዳለበት ወደ ሖሬሽ ሄዶ፣ . . . አበረታታው።” (1 ሳሙ. 23:15, 16) ሌሎችን ስትረዳ ለስለስ ባለ መንገድ ይሁን። ከልብ በመነጨ አሳቢነት የተነገሩ ቃላት ጥሩ ውጤት ያስገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪ መንፈሳዊ ወንድማችንን ወይም እህታችንን እንደገና የራሳችን ለማድረግ ትጋትና የታሰበበት ጥረት እንደሚያስፈልግ ኢየሱስ በምሳሌ በመጠቀም በግልጽ ተናግሯል። (ሉቃስ 15:4) ሌላውን ሰው ለማገዝ ልባዊ ፍላጎት ካለን በፍጥነት የሚታይ እድገት ባይኖርም እንኳ ሳንሰለች ለመርዳት እንገፋፋለን።
4 በመጽሐፍ ጥናታችን ውስጥ የሚገኙትን ወንድሞችና እህቶች ከእኛ ጋር አገልግሎት እንዲወጡ በመጋበዝ ቅድሚያውን ስንወስድ እንዴት የሚያበረታታ ይሆናል! አብሮን ይሖዋን የሚያመልክ ሰው በአገልግሎት እንዲካፈል በምንረዳበት ጊዜ በአምላክ አገልግሎት ይበልጥ እንዲሠራ ለማበረታታት አጋጣሚውን ልንጠቀምበት እንችላለን። በይሖዋ አገልግሎት አብረን የምናሳልፈው ይህን የመሰለ አስደሳች ጊዜ በተለይ ወደ ቀድሞ መንፈሳዊ አቋማቸው እየተመለሱ ላሉ ሰዎች የሚያበረታታ ነው።
5 ፍቅራዊ ዝግጅት:- ለተወሰነ ጊዜ በስብከቱ ሥራ ያልተካፈሉ ወይም ጉባኤ ያልመጡ ሰዎች እምነታቸውን ለማጠንከር ተጨማሪ እርዳታ ያስፈልጋቸው ይሆናል። እውነተኛው አንድ አምላክ ያስገኘው የአምልኮ አንድነት፣ ወደ ይሖዋ ቅረብ ወይም ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? እንደሚሉት ያሉ ጽሑፎችን ተጠቅሞ በግል መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ሊረዳው ይችላል። ግለሰቡ የተጠመቀ ስለሆነ በአብዛኛው ጥናቱ ረዘም ላለ ጊዜ መቀጠል የለበትም። የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ ከዚህ ዝግጅት ማን ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ በንቃት መከታተል አለበት።—የኅዳር 1998 እና የኅዳር 2000 የመንግሥት አገልግሎታችን የጥያቄ ሣጥኖችን ተመልከት።
6 ቀደም ሲል የተጠቀሰችው አና ሽማግሌዎች ከአንዲት ጎልማሳ እህት ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና ያቀረቡላትን ግብዣ በአድናቆት ተቀበለች። ይህች እህት እንደገና ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ያስፈለጋት አራት ጊዜ ማጥናት ብቻ ነበር። እንደገና የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ከመጀመሯም በላይ ይሖዋ አምላክን በሕዝብ ፊት የማወደስ ፍላጎቷ ተነሳስቷል። ጎልማሳዋ እህት፣ አና ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ለመካፈል በቂ ጥንካሬ እስክታገኝ ድረስ ወደ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቿ ይዛት በመሄድ በአገልግሎትም ጭምር ረድታታለች። አና መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቿን እንደገና ለመጀመር ያስፈለጋት በደግነት የሚሰጥ እርዳታ ብቻ ነበር!
7 እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ማበረታታት ለሁሉም በረከት ያስገኛል። እርዳታ የሚደረግለት ግለሰብ ወደ ይሖዋ መቅረብ በመቻሉና በድርጅቱ እንቅስቃሴ ውስጥ በመካተቱ ደስ ይለዋል። ሽማግሌዎች ይህን የመሰለ መንፈሳዊ እድገት ሲመለከቱ ደስ ይላቸዋል። (ሉቃስ 15:5, 6) የጉባኤው አባላትም አንዳቸው ለሌላው ፍቅራዊ ደግነት ስለሚያሳዩ አንድነት ይኖራቸዋል። (ቈላ. 3:12-14) በእርግጥም የቅርብ ረዳት የሆነውን ይሖዋን ለመምሰል የሚገፋፋ ጥሩ ምክንያት አለን!—ኤፌ. 5:1
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
1. የአንድ ሰው መንፈሳዊነት ሊዳከም የሚችለው እንዴት ነው?
2. ሁሉም ክርስቲያኖች ለሌሎች የቅርብ ረዳት መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?
3, 4. ሌሎችን መርዳት ምን ነገሮችን ይጨምራል? እንዲህ ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?
5. ሽማግሌዎች በአንዳንድ ሁኔታዎች ሥር ምን ዓይነት እርዳታ ሊሰጡ ይችላሉ?
6. አንዲት እህት በመንፈሳዊ ወደ ቀድሞ አቋሟ ለመመለስ የቻለችው እንዴት ነው?
7. ሌሎችን በመንፈሳዊ ማበረታታት ምን ውጤት ያስገኛል?