ሌሎች ሰዎች ከቤዛው እንዲጠቀሙ እርዷቸው
የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ሚያዝያ 12 ይከበራል
1. የአምላክ ሕዝቦች ለቤዛው ዝግጅት አድናቆት እንዳላቸው የሚያሳዩበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?
1 “በቃላት ሊገለጥ ስለማይቻል ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።” (2 ቆሮ. 9:15) እነዚህ ቃላት አምላክ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛ አማካኝነት ለሕዝቦቹ ላሳየው በጎነትና ፍቅራዊ ደግነት ያለንን የአድናቆት ስሜት ያሳያሉ። በተለይ ደግሞ ሚያዝያ 12 በሚከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ስንገኝ ይህ ስሜታችን በግልጽ ይታያል።
2. ከይሖዋ አገልጋዮች ጋር ሆነው የመታሰቢያውን በዓል የሚያከብሩት እነማን ናቸው? ከቤዛው ተጠቃሚ እንዲሆኑስ ምን ማድረግ ይገባቸዋል?
2 በየዓመቱ አሥር ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች ከይሖዋ አገልጋዮች ጋር ሆነው በመታሰቢያው በዓል ላይ ይገኛሉ። እንዲህ ማድረጋቸው በተወሰነ መጠን ለክርስቶስ መሥዋዕት አድናቆት እንዳላቸው ያሳያል። ይሁንና ከቤዛው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከተፈለገ በክርስቶስ መሥዋዕት ማመን ይገባቸዋል። (ዮሐ. 3:16, 36) ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን እምነት እንዲያዳብሩ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲኖራቸውና በሳምንታዊ የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ልናበረታታቸው እንችላለን። እስቲ ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች እንመልከት።
3. በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ የምንጋብዛቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
3 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች:- ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ በምትጋብዝበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተሰኘው መጽሐፍ አማካኝነት ጥናት ለማስጀመር ለምን አትሞክርም? ከገጽ 206-208 ላይ የሚገኘውን “የጌታ እራት—አምላክን የሚያስከብር በዓል” የሚለውን ርዕስ ተጠቅመህ ስለ መታሰቢያው በዓል ልታብራራለት እንደምትፈልግ ሐሳብ ማቅረብ ትችላለህ። ምናልባትም እዚያው በር ላይ እንደቆማችሁ በማስጠናት ይህን ርዕስ በአንድ አሊያም በሁለት ጊዜ ተመላልሶ መጠየቅ ልትሸፍነው ትችላለህ። ስለዚህ ጉዳይ ተነጋግራችሁ ከጨረሳችሁ በኋላ ግለሰቡ ምዕራፍ 5 ላይ በሚገኘው “ቤዛው—ከሁሉ የላቀ የአምላክ ስጦታ” በሚለው ርዕስ ላይ ለመወያየት ይፈልግ ይሆናል። አንዴ ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ካስጀመርከው በኋላ ወደ መጀመሪያዎቹ አራት ምዕራፎች ተመልሳችሁ አንድ በአንድ ተወያዩባቸው።
4. በመታሰቢያው በዓል ሰሞን መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እንዲጀምሩ እነማንን ማበረታታት እንችላለን?
4 ይህን አቀራረብ ተጠቅመን እነማንን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር እንችላለን? ከሥራ ባልደረቦችህ፣ አብረውህ ከሚማሩት ልጆች አሊያም ከጎረቤቶችህ መካከል አንዳንዶቹ እንዲህ ዓይነት ውይይት ማድረግ ይፈልጉ ይሆናል። ወንድሞች ደግሞ የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላቸው እህቶች ቤት ሄደው ከባሎቻቸው ጋር መወያየት ይችላሉ። የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ዘመዶችህንም ቢሆን ጥናት እንዲጀምሩ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል። ከዚህም በላይ በአንድ ወቅት በጉባኤው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የነበራቸው ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ ልዩ ጥረት ማድረግ እንፈልጋለን። (ሉቃስ 15:3-7) እነዚህ ሁሉ ከቤዛው ዝግጅት እንዲጠቀሙ ለመርዳት እንጣር።
5. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችና ፍላጎት ያሳዩ ሌሎች ሰዎች በሳምንታዊ የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ማበረታታት የምንችለው እንዴት ነው?
5 የጉባኤ ስብሰባዎች:- የመታሰቢያው በዓል ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችና ፍላጎት ያሳዩ ሌሎች ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገኙበት ስብሰባ ነው። ሆኖም ከሌሎቹ የጉባኤ ስብሰባዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው? የሚያዝያ 2005 የመንግሥት አገልግሎታችን የሚከተሉትን ሐሳቦች አስፍሯል:- “የሚቀጥለውን ሳምንት የሕዝብ ንግግር ርዕስ ንገራቸው። በመጠበቂያ ግንብ ጥናትና በመጽሐፍ ጥናት ወቅት የሚጠኑትን ጽሑፎች አሳያቸው። ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና የአገልግሎት ስብሰባ ምን እንደሆነ ግለጽላቸው። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል በሚኖርህ ጊዜ ከጥናቶችህ ጋር ልትለማመድ ትችላለህ። በስብሰባው ወቅት የቀረቡትን ጥሩ ጥሩ ነጥቦች አካፍላቸው። በጽሑፎቻችን ላይ ያሉትን ፎቶግራፎች በማሳየት በስብሰባው ላይ ምን እንደሚካሄድ የተወሰነ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እርዳቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ከጀመራችሁበት ጊዜ አንስቶ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ጋብዛቸው።”
6. ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ከቤዛው እንዲጠቀሙ ለመርዳት የሚያስችሉን ሁለት መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
6 አብዛኛውን ጊዜ እንደሚታየው ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት ካጠኑና በሳምንታዊው የጉባኤ ስብሰባ ላይ አዘውትረው ከተገኙ ፈጣን የሆነ መንፈሳዊ እድገት ያደርጋሉ። ስለሆነም በእነዚህ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉና ከአምላክ ስጦታዎች ሁሉ የላቀ ከሆነው ከቤዛው እንዲጠቀሙ እናበረታታቸው።