አድናቆት እንዳለን እናሳይ—የመታሰቢያው በዓል ሚያዝያ 17 ይከበራል
1. በመታሰቢያው በዓል ሰሞን መዝሙራዊው የተናገረውን የትኛውን ሐሳብ ማስታወሳችን የተገባ ነው?
1 መዝሙራዊው የይሖዋን ምሕረትና ማዳን በተደጋጋሚ ማየቱ “ስለ ዋለልኝ ውለታ ሁሉ፣ ለእግዚአብሔር ምን ልክፈለው?” እንዲል ገፋፍቶታል። (መዝ. 116:12) በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ግን አድናቆታቸውን እንዲገልጹ የሚያደርጋቸው ሌላ ተጨማሪ ምክንያት አላቸው። መዝሙራዊው ይህን ሐሳብ በመንፈስ ተመርቶ ከጻፈ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ይሖዋ ከሁሉ የላቀውን ስጦታ ማለትም ቤዛውን ለሰው ልጆች ሰጥቷል። በመሆኑም ሚያዝያ 17 የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር በምንዘጋጅበት በዚህ ወቅት አመስጋኝነታችንን እንድንገልጽ የሚያነሳሳን በቂ ምክንያት አለን።—ቆላ. 3:15
2. የቤዛውን ዝግጅት እንድናደንቅ የሚያነሳሱን አንዳንድ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?
2 ቤዛው የሚያስገኝልን በረከቶች፦ በቤዛው አማካኝነት “የኃጢአት ይቅርታ” ማግኘት ችለናል። (ቆላ. 1:13, 14) ይህ ደግሞ ይሖዋን በንጹሕ ሕሊና ለማምለክ ያስችለናል። (ዕብ. 9:13, 14) የመናገር ነፃነት ኖሮን ወደ አምላክ በጸሎት መቅረብ እንችላለን። (ዕብ. 4:14-16) በቤዛው ላይ እምነት እንዳላቸው በተግባር የሚያሳዩ ሰዎች ለዘላለም የመኖር ታላቅ ተስፋ ከፊታቸው ተዘርግቶላቸዋል!—ዮሐ. 3:16
3. ለቤዛው ያለንን አድናቆት ለይሖዋ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
3 አድናቆታችንን መግለጽ የምንችልበት መንገድ፦ ለቤዛው ያለንን ጥልቅ አድናቆት የምናሳይበት አንዱ መንገድ ለመታሰቢያው በዓል ተብሎ የተዘጋጀውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ በየዕለቱ ማንበብና ባነበብነው ላይ ማሰላሰል ነው። የካቲት 1, 2011 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣው “ትልቅ ቦታ ለሚሰጠው ቀን ተዘጋጅተሃል?” የሚለው ርዕስ ለዚህ እንዲረዳን ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በተጨማሪም ለቤዛው ምን ያህል አድናቆት እንዳለን የሚያሳይ ልባዊ ጸሎት ወደ ይሖዋ ማቅረብ እንችላለን። (1 ተሰ. 5:17, 18) የኢየሱስን ትእዛዝ በመከተል በሞቱ መታሰቢያ ላይ መገኘታችንም አመስጋኝ መሆናችንን ያሳያል። (1 ቆሮ. 11:24, 25) ከዚህም በላይ በተቻለን መጠን ብዙ ሰዎች በበዓሉ ላይ አብረውን እንዲገኙ በመጋበዝ ይሖዋ ያሳየውን ታላቅ ፍቅር ማንጸባረቅ እንችላለን።—ኢሳ. 55:1-3
4. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል?
4 አድናቂ የሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች የመታሰቢያውን በዓል ከሌሎች ስብሰባዎች ሁሉ ይበልጥ ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። በዓሉን ለማክበር የምናደርገው ይህ ስብሰባ በዓመቱ ውስጥ በጣም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ስብሰባ ነው! የመታሰቢያው በዓል እየቀረበ ሲመጣ የእኛም ቁርጥ ውሳኔ “ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ ውለታውንም ሁሉ አትርሺ” በማለት እንደጻፈው እንደ መዝሙራዊው መሆን ይኖርበታል።—መዝ. 103:2