“ይህን ሁልጊዜ . . . አድርጉት”—የመታሰቢያው በዓል መጋቢት 27, 2004 (ሚያዝያ 5, 2012) ይከበራል
1. የመታሰቢያው በዓል ከፍ ያለ ግምት ሊሰጠው የሚገባው ለምንድን ነው?
1 “ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት።” (ሉቃስ 22:19) ኢየሱስ ይህን ሐሳብ በመናገር የእሱን መሥዋዕታዊ ሞት እንዲያስቡ ተከታዮቹን አዟቸዋል። ቤዛው ከፍተኛ ጥቅም ያስገኘ በመሆኑ ክርስቲያኖች የመታሰቢያው በዓል ለሚከበርበት ዕለት ከፍ ያለ ግምት ይሰጣሉ። መጋቢት 27, 2004 የምናከብረው በዓል እየተቃረበ እንደመሆኑ መጠን ይሖዋ ላደረገልን ነገር ያለንን አመስጋኝነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?—ቆላ. 3:15
2. በማጥናትና በማሰላሰል ለመታሰቢያው በዓል ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
2 ዝግጅት ማድረግ፦ ከፍ ያለ ግምት ለምንሰጣቸው ነገሮች ቅድመ ዝግጅት እንደምናደርግ የታወቀ ነው። በመሆኑም በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን፣ ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፋቸው የመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ ስለተፈጸሙት ነገሮች በማጥናትና በዘገባዎቹ ላይ በማሰላሰል ለመታሰቢያው በዓል ልባችንን ማዘጋጀት እንችላለን። (ዕዝራ 7:10) እነዚህ ዘገባዎች ከሚገኙባቸው ጥቅሶች የተወሰኑትን በቀን መቁጠሪያ እና ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር በተባለው ቡክሌት ላይ ማግኘት የሚቻል ሲሆን የየካቲት 1, 2011 መጠበቂያ ግንብ ደግሞ በገጽ 23 እና 24 ላይ በዛ ያሉ ጥቅሶችን እንዲሁም ታላቅ ሰው በተባለው መጽሐፍ ላይ እነዚህ ጥቅሶች የተብራሩባቸውን ምዕራፎች ይዟል።
3. ለመታሰቢያው በዓል ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
3 መስበክ፦ አድናቆታችንን ማሳየት የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ አቅማችን የፈቀደውን ያህል በአገልግሎት ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ ነው። (ሉቃስ 6:45) ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ የምንጋብዝበት ዓለም አቀፋዊ ዘመቻ ቅዳሜ፣ መጋቢት 8, 2004 (መጋቢት 17, 2012) ይጀምራል። ፕሮግራማችሁን በማስተካከል በአገልግሎት ከበፊቱ የበለጠ ጊዜ ማሳለፍ ወይም ረዳት አቅኚ ሆናችሁ ማገልገል ትችላላችሁ? በሚቀጥለው የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ላይ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ለምን አትወያዩም?
4. በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘት ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
4 በየዓመቱ በሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ መገኘት ከፍተኛ ጥቅም ያስገኝልናል። ይሖዋ አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ በመስጠት ስላሳየን ደግነት ማሰላሰላችን ለአምላክ ያለን ፍቅር እንዲሁም ደስታችን እንዲጨምር ያደርጋል። (ዮሐ. 3:16፤ 1 ዮሐ. 4:9, 10) ይህ ደግሞ ከዚህ በኋላ ለራሳችን እንዳንኖር ግድ ይለናል። (2 ቆሮ. 5:14, 15) እንዲሁም በሕዝብ ፊት ይሖዋን የማወደስ ፍላጎታችን እንዲጨምር ያደርጋል። (መዝ. 102:19-21) በእርግጥም የይሖዋ አገልጋዮች፣ መጋቢት 27, 2004 የሚከበረው በዓል የኢየሱስን ‘ሞት ለማወጅ’ የሚያስችል አጋጣሚ ስለሚሰጣቸው ይህን ቀን በጉጉት መጠባበቃቸው ምንም አያስገርምም።—1 ቆሮ. 11:26