የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር በደስተኛ ልብ ዝግጅት አድርጉ
1. የመታሰቢያው በዓል ሰሞን ምን ለማድረግ ግሩም አጋጣሚ ይሰጠናል?
1 ማክሰኞ፣ መጋቢት 26 የሚከበረው የመታሰቢያው በዓል አምላክ እኛን ለማዳን ባደረገው ዝግጅት ለመደሰት ግሩም አጋጣሚ ይሰጠናል። (ኢሳ. 61:10) በዓሉን ከማክበራችን በፊትም የደስተኝነት መንፈስ ማሳየታችን ለበዓሉ በደንብ ለመዘጋጀት ይረዳናል። በምን መንገድ?
2. ለመታሰቢያው በዓል ዝግጅት እንድናደርግ የሚያነሳሳን ምንድን ነው?
2 ለበዓሉ መዘጋጀት፦ የጌታ ራት ትልቅ ክብደት የሚሰጠው ሆኖም ቀለል ያለ ዝግጅት ነው። ያም ቢሆን አስፈላጊ የሆኑ ጥቃቅን ነገሮች እንዳይረሱ አስቀድሞ ዕቅድ ማውጣት ይጠይቃል። (ምሳሌ 21:5) በዓሉ የሚከበርበት አመቺ የሆነ ቦታና ፕሮግራሙ የሚጀምርበት ሰዓት መወሰን አለበት። እንዲሁም ምሳሌያዊው ቂጣና ወይን በተገቢው መንገድ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም አዳራሹ መጽዳትና በሚገባ መዘጋጀት ይኖርበታል። ንግግሩን የሚያቀርበውም ወንድም ጥሩ ዝግጅት ማድረግ አለበት፤ እንዲሁም አስተናጋጆችም ሆኑ ቂጣውንና ወይኑን የሚያዞሩ ወንድሞች በሚገባ መደራጀት አለባቸው። እስካሁን ድረስ አብዛኛው ዝግጅት ተጠናቅቆ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ለቤዛው ያለን አድናቆት ለዚህ ቅዱስ በዓል በደንብ እንድንዘጋጅ ያነሳሳናል።—1 ጴጥ. 1:8, 9
3. ለጌታ ራት ልባችንን ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
3 ልብን ማዘጋጀት፦ የመታሰቢያው በዓል ለእኛ ያለውን ትርጉም በሚገባ ለመረዳት ልባችንን ማዘጋጀታችን አስፈላጊ ነው። (ዕዝራ 7:10) ከዚህ አንጻር በመታሰቢያው በዓል ሰሞን የሚደረገውን ልዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ለማንበብ እንዲሁም ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ባሳለፋቸው የመጨረሻ ቀናት ላይ ለማሰላሰል ጊዜ መመደባችን የተገባ ነው። ኢየሱስ ባሳየው የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ላይ ማሰላሰላችን እሱን እንድንመስል ያነሳሳናል።—ገላ. 2:20
4. ቤዛው ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል ይበልጥ የሚያስደስትህ የትኛው ነው?
4 የክርስቶስ ሞት የይሖዋ ሉዓላዊነት እንዲረጋገጥ ያደረጋል። ደግሞም የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ያወጣል። (1 ዮሐ. 2:2) እንዲሁም ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረንና የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ መንገድ ይከፍታል። (ቆላ. 1:21, 22) በተጨማሪም ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን የገባነውን ቃል እስከ መጨረሻው ጠብቀን እንድንኖር ይረዳናል፤ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሆነን እንድንጸናም ያደርገናል። (ማቴ. 16:24) ለመጪው የመታሰቢያ በዓል ስትዘጋጁም ሆነ በበዓሉ ላይ ስትገኙ ይበልጥ ደስተኞች እንድትሆኑ ምኞታችን ነው!