“ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ሚያዝያ 2 ይከበራል
1. ሚያዝያ 2, 2007 ልዩ ቀን የሆነው ለምንድን ነው?
1 ሚያዝያ 2, 2007 (መጋቢት 24, 1999) በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የኢየሱስን መሥዋዕታዊ ሞት ለማክበር አንድ ላይ ይሰበሰባሉ። ኢየሱስ የሞተው ሰይጣን ዲያብሎስ ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ነው በማለት ያስነሳው ክርክር ሐሰት መሆኑን በማረጋገጥ በሰማይ የሚኖረውን አባቱን ሉዓላዊነት ለማስከበር ሲል ነው። (ኢዮብ 2:1-5) የጌታ እራት ኢየሱስ ፍጹምና ኃጢአት የሌለበት ሰው ሆኖ በመሞት ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ መስጠቱን’ ያስታውሰናል። (ማቴ. 20:28) በመሆኑም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት አዟቸዋል። (ሉቃስ 22:19) ለዚህ ውድ የአምላክ ስጦታ ያለህ አድናቆት ከሁሉ የላቀ የፍቅር መግለጫ የሆነውን የኢየሱስን ሞት ለማሰብ ከአሁኑ ዝግጅት እንድታደርግ አያነሳሳህም?—ዮሐ. 3:16
2. ለመታሰቢያው በዓል ልባችንን ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
2 ልባችሁን አዘጋጁ:- ኢየሱስ የምድራዊ ሕይወቱን የመጨረሻ ቀናት እንዴት እንዳሳለፋቸው በማንበብ የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር ልባችንን ማዘጋጀት እንችላለን። (ዕዝራ 7:10 የ1954 ትርጉም) በዚህ ረገድ እኛን ለመርዳት ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2007 በተባለው ቡክሌትና በ2007 የቀን መቁጠሪያ ላይ ልዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ወጥቶልናል። ይህ የንባብ ፕሮግራም በዘመናችን የቀን አቆጣጠር መሠረት ኢየሱስ በሞተበት ሰሞን የተከናወኑትን ነገሮች ይዟል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ላይ የተጠቀሱት ቀናት በአይሁዳውያን የቀን አቆጣጠር ላይ የተመሠረቱ ሲሆን አይሁዳውያን አንድ ቀን የሚሉት ምሽት ላይ ፀሐይ ከምትጠልቅበት ሰዓት አንስቶ በሚቀጥለው ቀን እንደገና እስከምትጠልቅበት ሰዓት ድረስ ያለውን ጊዜ ነው። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም የተዘጋጀው ይህን የቀን አቆጣጠር ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ መከለሳችን እንዲሁም አምላክ ባሳየን ጥልቅ ፍቅር ላይ በጸሎት ማሰላሰላችን ከመታሰቢያው በዓል ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚዎች እንድንሆን ይረዳናል።
3. ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችና የቀዘቀዙ ወንድሞች ከመታሰቢያው በዓል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?
3 ሌሎች በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ጋብዙ:- በየካቲት የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ ላይ ሰዎችን በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ የሚደረግ ልዩ ዘመቻ እንደሚኖር ተገልጿል። በዚህ ዘመቻ ላይ በሚገባ ለመሳተፍ ዝግጅት አድርገሃል? ለመጋበዝ ያሰብካቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር ይዘሃል? በዝርዝሩ ውስጥ የያዝካቸውን ሰዎች ስለ ጉዳዩ ነግረሃቸዋል? የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ምሽት ቀደም ብለህ በቦታው በመገኘት የጋበዝካቸውን ሰዎች ጨምሮ ሌሎችን ለመቀበል ዝግጅት አድርግ። አብረውህ እንዲቀመጡ በማድረግ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም መዝሙር ልታሳያቸው ትችላለህ። እንግዶችህን በጉባኤህ ከሚገኙት ወንድሞችና እህቶች ጋር አስተዋውቃቸው። ከበዓሉ በኋላ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ካሉ ለመመለስ ጥረት አድርግ፤ በተጨማሪም ሚያዝያ 15, 2007 በሚሰጠው ልዩ የሕዝብ ንግግር ላይ እንዲገኙ ጋብዛቸው። በተለይ ሽማግሌዎች ቀደም ሲል በጉባኤ ውስጥ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደርጉ የነበሩ አሁን ግን የቀዘቀዙ ወንድሞች በመታሰቢያው በዓልና በልዩ የሕዝብ ንግግሩ ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል።
4. በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙ ሰዎች መንፈሳዊ እድገት ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?
4 ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችና የቀዘቀዙ ወንድሞች እድገት እንዲያደርጉ እርዷቸው:- የመታሰቢያውን በዓል ንግግር የሚያቀርበው ወንድም ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር ስለተደረገው ዝግጅት በአጭሩ በመግለጽ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ስለ ይሖዋ መማራቸውን እንዲቀጥሉ ያበረታታል። ይህን ሐሳብ መሠረት በማድረግ ሰዎቹ ተጨማሪ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ልትረዳቸው እንደምትፈልግ ልትገልጽላቸው ትችላለህ። በአሁኑ ወቅት የማያጠኑ ከሆነ ከበዓሉ ብዙም ሳይቆይ ተመልሰህ በመሄድ መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ክፍያ እንዴት እንደምናስጠና አሳያቸው። እነዚህ አዲሶች መንፈሳዊ እድገት ማድረግ እንዲችሉ በጉባኤ ስብሰባዎችም ላይ መገኘት ይኖርባቸዋል። (ዕብ. 10:24, 25) ስለሆነም በስብሰባዎች ላይ አዘውትረው እንዲገኙ አበረታታቸው። ሽማግሌዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙትን የቀዘቀዙ ክርስቲያኖች እንደገና ሄደው በመጠየቅ በበዓሉ ዕለት ለቀረበው ንግግር የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡ ሊያበረታቷቸው ይገባል። ይህ ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ያደርጉ የነበረውን እንቅስቃሴ እንደገና እንዲጀምሩ ሊያበረታታቸው ይችላል።
5. የመታሰቢያውን በዓል ማክበራችን ምን ውጤት ይኖረዋል?
5 የመታሰቢያው በዓል ይሖዋና ኢየሱስ ያደረጉልንን ነገር በቁም ነገር የምናሰላስልበትን አጋጣሚ ይከፍትልናል። እንዲህ ዓይነቱ ማሰላሰል ለእነርሱ ያለንን ፍቅር የሚጨምርልን ሲሆን መልካም ባሕርይ እንድናዳብርም ይረዳናል። (2 ቆሮ. 5:14, 15፤ 1 ዮሐ. 4:11) ‘የጌታን ሞት ለምንናገርበት’ ለዚህ ልዩ በዓል ራሳችንንም ሆነ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ማዘጋጀት ያለብን አሁን ነው።—1 ቆሮ. 11:26