በቁም ነገር ሊታሰብበት የሚገባ የቪዲዮ ፊልም
“ይህ ቪዲዮ ቆም ብላችሁ እንድታስቡ ያደርጋችኋል!”
“ይህ ቪዲዮ በጥልቅ ነክቶኛል!”
“ስሜቴ በጥልቅ ተነክቷል!”
1 የወጣቶች ጥያቄ—እውነተኛ ጓደኞች ማፍራት የምችለው እንዴት ነው? የተሰኘውን የቪዲዮ ፊልም ለመጀመሪያ ጊዜ ስትመለከት እንደዚህ ተሰምቶህ ነበር? ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አንድ ወጣት በመረጣቸው ጓደኞች ምክንያት በሕይወቱ ውስጥ ችግር አጋጥሞት ነበር። ለእውነት የነበረውን ፍላጎትና ከይሖዋ ጋር የነበረውን ዝምድና እንዲያጣ አድርገውት ነበር። ከዚያም እውነተኛ ጓደኞች የሚለው የቪዲዮ ፊልም ወጣ። እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ቪዲዮውን ደጋግሜ በማይበት ጊዜ እንባዬ በጉንጮቼ ላይ ኮለል እያለ ይወርድ ነበር። በትክክለኛው ጊዜ እርዳታ በማግኘቴ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።” ይህ የቪዲዮ ፊልም በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ለውጥ እንዲያደርግና ጥሩ ጓደኞች እንዲይዝ ገፋፍቶታል። “[የዚህ ቪዲዮ አዘጋጆች፣] ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ነገሮች እንደምታውቁ በግልጽ ለማየት ይቻላል” በማለት አክሎ ተናግሯል። ወላጆችና ወጣቶች ይህንን ቪዲዮ በቀጣዩ የቤተሰብ ጥናታችሁ ወቅት ለምን በድጋሚ አትመለከቱትም? በእያንዳንዱ የፊልሙ ክፍል ላይ በማቆም በሚቀጥሉት አንቀጾች ውስጥ ባሉት ጥያቄዎች ላይ የልባችሁን አውጥታችሁ በግልጽ ተወያዩባቸው።
2 መግቢያ:- እውነተኛ ጓደኛ ማለት ምን ማለት ነው?—ምሳሌ 18:24
3 ለጓደኝነት እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች:- የመገለልን ስሜት ማሸነፍ የምትችለው እንዴት ነው? (ፊልጵ. 2:4) የባሕርይ ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን ያለብህ ለምንድን ነው? እንዲህ እንድታደርግ ማን ሊረዳህ ይችላል? ተጨማሪ ጓደኞች ለማፍራት የሚያስችሉህ ምን አጋጣሚዎች አሉ? እነዚህን ጓደኞች ልታገኝ የምትችለውስ የት ነው?—2 ቆሮ. 6:13
4 የአምላክ ወዳጅ መሆን:- ከአምላክ ጋር የተቀራረበ ወዳጅነት መመሥረት የምትችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጉ የሚክስ የሆነውስ ለምንድን ነው? (መዝ. 34:8) ከአምላክ ጋር ያለህን ወዳጅነት ይበልጥ ሊያጠናክሩልህ የሚችሉት እነማን ናቸው?
5 መጥፎ ጓደኞች:- መጥፎ ጓደኞች ሊባሉ የሚችሉት እነማን ናቸው? (1 ቆሮ. 15:33) መጥፎ ጓደኞች አንድን ሰው ወደ መንፈሳዊ ውድቀት ሊመሩት የሚችሉት እንዴት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው የዲና ታሪክ ምን ትማራለህ?—ዘፍ. 34:1, 2, 7, 19
6 ዘመናዊ ድራማ:- ታራ በብቸኝነት ስሜት የተጠቃችው እንዴት ነበር? ከዓለማዊ ወጣቶች ጋር የነበራት ቅርርብ ምንም ጉዳት እንደሌለው ለማሳመን የሞከረችው እንዴት ነው? እነዚህ ጓደኞቿ ለምን ዓይነት አደጋዎች እንድትጋለጥ አደረጓት? ወላጆቿ የነበረችበትን አደገኛ ሁኔታ ለመመልከት ያልቻሉት ለምን ነበር? ሆኖም በመንፈሳዊ እንድታገግም የረዷት በምን ዓይነት ዝንባሌ ነበር? አንዲት አቅኚ እህት ለታራ እውነተኛ ጓደኛ ልትሆንላት የቻለችው እንዴት ነው? ክርስቲያኖች በምሳሌ 13:20 እና በኤርምያስ 17:9 ላይ የሚገኙትን ምክሮች መከተል ያለባቸው ለምንድን ነው? ታራ ምን ጠቃሚ ትምህርት አግኝታለች?
7 መደምደሚያ:- ከዚህ የቪዲዮ ፊልም ምን ትምህርቶችን አግኝተሃል? ሌሎችን ለመርዳት እንዴት ልትጠቀምበት ትችላለህ?—መዝ. 71:17