የፈቃደኝነት መንፈስ ማሳየት በረከት ያስገኛል
1. ዳዊትና ነህምያ የፈቃደኝነት መንፈስ ያሳዩት እንዴት ነው?
1 ጎልያድ የእስራኤልን ሠራዊት በተገዳደረ ጊዜ ከሠራዊቱ መካከል አንዱ እርሱን ለመግጠም ፈቃደኛ ሊሆን ይችል ነበር። ሆኖም ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነው የውጊያ ልምድ ያልነበረው አንድ ትንሽ እረኛ ነበር። (1 ሳሙ. 17:32) ከምርኮ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት አይሁዳውያን የፈረሱትን ቅጥሮች ሳይገነቡ በቀሩበት ጊዜ የፋርስ ንጉሥ ጠጅ አሳላፊ የነበረ አንድ ሰው በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ያለውን የተከበረ ቦታ በፈቃደኝነት በመተው ሥራውን ለማደራጀት ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዟል። (ነህ. 2:5) እነዚህ ሁለት ሰዎች ማለትም ዳዊትና ነህምያ የፈቃደኝነት መንፈስ በማሳየታቸው ይሖዋ ባርኳቸዋል።—1 ሳሙ. 17:45, 50፤ ነህ. 6:15, 16
2. ክርስቲያኖች የፈቃደኝነት መንፈስ ማሳየት ያለባቸው ለምንድን ነው?
2 በዛሬው ጊዜ፣ የፈቃደኝነት መንፈስ ከዓለም ላይ ጠፍቷል። በዚህ “በመጨረሻው ዘመን” ሰዎች በሥራ የተጠመዱ ከመሆናቸውም ሌላ ብዙዎች “ራሳቸውን የሚወዱ” ናቸው። (2 ጢሞ. 3:1, 2) በመሆኑም አንድ ሰው በግል ጉዳዮቹ ከመጠመዱ የተነሳ በፈቃደኝነት ሌሎችን መርዳት የሚችልበት አጋጣሚ እያለ ይህን ሳያደርግ ሊቀር ይችላል። ሆኖም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ሌሎችን ለመርዳት ቀዳሚ የነበረውን ኢየሱስን መምሰል እንፈልጋለን። (ዮሐ. 5:5-9፤ 13:12-15፤ 1 ጴጥ. 2:21) የፈቃደኝነት መንፈስ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ምንስ በረከት እናገኛለን?
3. የፈቃደኝነት መንፈስ ለጉባኤ ስብሰባዎች አስተዋጽኦ የሚያበረክተው እንዴት ነው?
3 ወንድሞቻችንን በማገልገል:- በጉባኤ ውስጥ የአድማጮችን ተሳትፎ የሚጠይቁ ክፍሎች ሲቀርቡ ሐሳብ ለመስጠት ፈቃደኞች በመሆን ለሌሎች “መንፈሳዊ ስጦታ” ማካፈል እንችላለን። (ሮሜ 1:11) በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት ይሖዋን ያስከብረዋል እንዲሁም እውነት በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ ሥር እንዲሰድ ብሎም ስብሰባዎች ይበልጥ አስደሳች እንዲሆኑልን ያደርጋል። (መዝ. 26:12) በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል የተሰጠው ሰው ማቅረብ ሳይችል በሚቀርበት ጊዜ በፈቃደኝነት ክፍሉን ማቅረብ እንችላለን። ይህ ደግሞ የማስተማር ችሎታችንን ያሻሽልልናል።
4. የፈቃደኝነት መንፈስ ማሳየት የምንችልባቸው ምን ሌሎች መንገዶች አሉ?
4 ወንድሞች በጉባኤ ውስጥ ያሉትን አንዳንድ ኃላፊነቶች ለመሸከም በመጣጣር የፈቃደኝነት መንፈስ ማሳየት ይችላሉ። (ኢሳ. 32:2፤ 1 ጢሞ. 3:1) ትላልቅ ስብሰባዎች በተቃና ሁኔታ መካሄድ እንዲችሉ ሁላችንም በተለያዩ የሥራ ምድቦች ውስጥ በፈቃደኝነት በመካፈል የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን። ከተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ጋር አብረን ለማገልገልም ይሁን እነርሱን ምግብ ለመጋበዝ ፈቃደኛ መሆናችን ‘እርስ በርሳችን ለመበረታታት’ ያስችለናል። (ሮሜ 1:12) አባት ለሌላቸው ልጆች፣ ለመበለቶች፣ ለታመሙና አቅመ ደካማ ለሆኑ፣ ትንንሽ ልጆች ላላቸው እናቶች እንዲሁም በጉባኤያችን ውስጥ ለሚገኙ ሌሎች ወንድሞችና እህቶች ጠቃሚ እርዳታ ስናበረክት ደስታ የምናጭድ ከመሆኑም ሌላ የይሖዋን ሞገስ እናገኛለን።—ምሳሌ 19:17፤ ሥራ 20:35
5. ከመንግሥት አዳራሽ ጋር በተያያዘ ፈቃደኝነትን የሚጠይቁ ምን ነገሮች አሉ?
5 ጊዜያችንንና ጉልበታችንን በፈቃደኝነት የምንሰጥበት ሌላው መንገድ የመንግሥት አዳራሹን በማጽዳቱና በመጠገኑ ሥራ ላይ በመካፈል ነው። ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ሰዎች ወደ እውነት እየመጡ በመሆናቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾችን መገንባት አስፈላጊ ሆኗል፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ ፈቃደኛ ሠራተኞች ያስፈልጋሉ። አንድ ባልና ሚስት የግንባታ ሙያ ባይኖራቸውም እንኳ እርዳታ ለማበርከት ራሳቸውን አቀረቡ። እነዚህ ባልና ሚስት በጊዜ ሂደት ሥልጠና የተሰጣቸው ሲሆን አሁን በግንባታው ሥራ እርዳታ እያበረከቱ ነው። ሚስትየዋ እንዲህ ትላለች:- “ከሌሎች ጋር አብረን መሥራታችን የቅርብ ወዳጅነት ለመመሥረት አስችሎናል። በቀኑ መገባደጃ ላይ ሰውነታችን ቢዝልም በመንፈሳዊ ግን እንታደሳለን።”
6. የስብከቱ ሥራችን በፈቃደኝነት ከምንሠራቸው ሥራዎች ሁሉ የላቀ የሆነው ለምንድን ነው?
6 በስብከቱ ሥራ:- በዛሬው ጊዜ በፈቃደኝነት ከምንሠራቸው ሥራዎች ሁሉ የላቀውን ቦታ የሚይዘው የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩ ሥራ ነው። ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር እንዲያስተውሉና ተግባራዊ እንዲያደርጉ ስንረዳቸው ሕይወታቸው ዓላማ ይኖረዋል፤ እንዲሁም መጥፎ ልማዶቻቸውን ለማሸነፍ የሚያስችላቸውን ኃይል ያገኛሉ። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ የሚናገረውን አስደሳች ተስፋ ይማራሉ። ሌሎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲማሩ በመርዳት ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኘውን አስደሳች አገልግሎት በፈቃደኝነት እናከናውናለን። (ዮሐ. 17:3፤ 1 ጢሞ. 4:16) በዚህ ሥራ ይበልጥ ለመካፈል ሁኔታችን የሚፈቅድልን ከሆነ ረዳት ወይም የዘወትር አቅኚ ሆኖ ማገልገል፣ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት አካባቢ መሄድ፣ ልዩ አቅኚ መሆን አሊያም ደግሞ ሌላ ቋንቋ መማር እንችላለን።
7. በተለይ በዛሬው ጊዜ የፈቃደኝነት መንፈስ ማሳየት እጅግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
7 ንጉሥ ዳዊት፣ መሲሑ መግዛት በሚጀምርበት ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች ‘በገዛ ፈቃዳቸው’ ራሳቸውን እንደሚያቀርቡ ትንቢት ተናግሯል። (መዝ. 110:3) ይሖዋ የመጨረሻውን መንፈሳዊ የመከር ሥራ እያፋጠነ ባለበት በዚህ ጊዜ በፈቃደኝነት የሚሠራ ብዙ ሥራ አለ። (ኢሳ. 60:22) አንተስ “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ” ብለሃል? (ኢሳ. 6:8) እውነት ነው፣ የፈቃደኝነት መንፈስ በማሳየት ይሖዋን እናስደስታለን፤ እንዲሁም የተትረፈረፉ በረከቶችን እናጭዳለን።