“ለደከመው ብርታት ይሰጣል”
1 ሁላችንም አልፎ አልፎ የድካም ስሜት ይጫጫነናል። ድካም የሚመጣው ከሥራ ወይም ከሌላ ዓይነት አካላዊ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን በዚህ “የሚያስጨንቅ ጊዜ” ውስጥ ከሚያጋጥሙን የተለያዩ ችግሮች ጭምር ነው። (2 ጢሞ. 3:1) የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን በአገልግሎታችን እንዳንደክም የሚረዳንን መንፈሳዊ ጥንካሬ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ‘ታላቅ ኃይል’ ባለው በይሖዋ በመታመን ነው። (ኢሳ. 40:26) ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ነገሮች የሚያውቅ ከመሆኑም በላይ እኛን ለመርዳት ልባዊ ፍላጎት አለው።—1 ጴጥ. 5:7
2 ይሖዋ እኛን ለመርዳት ያደረጋቸው ዝግጅቶች:- ይሖዋ አጽናፈ ዓለምን ለመፍጠር በተጠቀመበት ከፍተኛ ኃይል ማለትም በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ያበረታናል። የአምላክ መንፈስ ድካም በሚሰማን ጊዜ ‘ኃይላችንን እንድናድስ’ ይረዳናል። (ኢሳ. 40:31) እስቲ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ክርስቲያናዊ ግዴታዎቼን ለመወጣት የሚያስችለኝን ጥንካሬ ለማግኘት ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠኝ ለመጨረሻ ጊዜ የጸለይኩት መቼ ነው?’—ሉቃስ 11:11-13
3 በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል በየቀኑ፣ ስናነብ ባነበብነው ላይ ስናሰላስል እንዲሁም ክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችንን አዘውትረን እያጠናን በመንፈሳዊ ስንመገብ “በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ” ሕያው ዛፍ እንሆናለን።—መዝ. 1:2, 3
4 በተጨማሪም ይሖዋ “የብርታት ምንጭ” ሊሆኑልን በሚችሉት የእምነት አጋሮቻችን ይጠቀማል። (ቈላ. 4:10, 11 NW) እነዚህ ወንድሞቻችን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስንገናኝ ከእኛ ጋር በሚያደርጉት የሚያንጽ ጭውውት እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ በሚሰጧቸው ሐሳቦችና ንግግሮች አማካኝነት ያበረቱናል። (ሥራ 15:32) በተለይ ደግሞ የጉባኤ ሽማግሌዎች መንፈሳዊ እርዳታና የሚያነቃቃ ማበረታቻ ይሰጡናል።—ኢሳ. 32:1, 2
5 አገልግሎት:- የድካም ስሜት ቢጫጫንህ እንኳ ለሌሎች መስበክህን አታቋርጥ! በአገልግሎት አዘውትሮ መካፈል እንደ ሌሎች በርካታ እንቅስቃሴዎች ለድካም የሚዳርግ ሳይሆን እውነተኛ እረፍት የሚያስገኝ ነው። (ማቴ. 11:28-30) ምሥራቹን መስበካችን ትኩረታችን በአምላክ መንግሥት ላይ እንዲያርፍ እንዲሁም ዘላለማዊነትንና ከዚያ ጋር ተያይዘው የሚመጡትን በረከቶች ዘወትር እንድናስብ ያደርገናል።
6 ይህ ክፉ ሥርዓት ከመጥፋቱ በፊት ብዙ የምንሠራው ሥራ አለ። በመሆኑም ‘አምላክ በሚሰጠን ብርታት’ በመታገዝ በአገልግሎታችን እስከ መጨረሻው እንድንጸና የሚገፋፋን በቂ ምክንያት አለን። (1 ጴጥ. 4:11) ይሖዋ ‘ለደከመው ብርታትን ስለሚሰጥ’ በእርሱ እርዳታ ሥራችንን ዳር እናደርሳለን።—ኢሳ. 40:29