ለአገልግሎት ያለን ቅንዓት እንዳይቀዘቅዝ እንጠንቀቅ
1 ከ1992 ጀምሮ ባለው በእያንዳንዱ ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት በመካፈል ከአንድ ቢሊዮን ሰዓት በላይ አሳልፈዋል። እንዲህ የመሰለ አስደናቂ ውጤት እንዲገኝ አነስተኛም ቢሆን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ በመቻላችን ምንኛ ደስተኞች ነን!—ማቴ. 28:19, 20
2 እርግጥ ነው፣ ለዚህ ሁሉ ሊመሰገንና ሊወደስ የሚገባው በዚህ “በመጨረሻው ዘመን” በአገልግሎታችን እንድንቀጥል አስፈላጊውን ድጋፍ ያደረገልን ይሖዋ ነው። (2 ጢሞ. 3:1) በዚህ ታላቅ ሥራ በቅንዓት መካፈላችንን ለመቀጠል ከእኛ የሚፈለገው ምንድን ነው?
3 በቅንዓት እንድናገለግል የሚያነሳሳን ምክንያት:- የአምላክን መንግሥት በመስበኩ ሥራ በቅንዓት እንድንካፈል የሚያነሳሳን ለአምላክና ለሰዎች ያለን ጥልቅ ፍቅር እንዲሁም ራሳችንን ስንወስን የገባነውን ቃል ለመፈጸም ያለን ልባዊ ፍላጎት ነው። (ማቴ. 22:37-39፤ 1 ዮሐ. 5:3) ፍቅር በስብከቱ ሥራ ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ ስንል አስፈላጊውን መሥዋዕትነት ሁሉ እንድንከፍል ይገፋፋናል።—ሉቃስ 9:23
4 ቅንዓታችን እንዳይቀዘቅዝ እንጣር:- ባላጋራችን ዲያብሎስ ለአገልግሎት ያለንን ቅንዓት ለማቀዝቀዝ የማያደርገው ጥረት የለም። ሰይጣን እኛን ተስፋ ለማስቆረጥ ከሚጠቀምባቸው ነገሮች መካከል በክልላችን ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ግዴለሽነት፣ ትኩረት የሚከፋፍሉ የዓለም ሁኔታዎች፣ ዕለታዊ ኑሮን ለማሸነፍ የምናደርገው ትግል እንዲሁም ጤንነታችን እያሽቆለቆለ መሄዱ የሚፈጥርብን ጭንቀት ይገኙበታል።
5 በመሆኑም ቅንዓታችን እንዳይቀዘቅዝ ብርቱ ጥረት ልናደርግ ይገባናል። ‘የቀድሞውን ፍቅራችንን’ እንደገና ማቀጣጠላችን አስፈላጊ ነው። ይህንን ማድረግ የምንችለው የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር በማንበብና በማሰላሰል እንዲሁም ይሖዋ እምነታችንን ለማጠናከር ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል ከሚያቀርብልን መንፈሳዊ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ነው።—ራእይ 2:4፤ ማቴ. 24:45 የ1954 ትርጉም፤ መዝ. 119:97
6 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በግልጽ እንደሚያሳዩት ክፉ ሰዎች የሚጠፉበት የይሖዋ ቀን በጣም እየቀረበ ነው። (2 ጴጥ. 2:3፤ 3:10) ይህን በአእምሯችን ይዘን በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም በመካሄድ ላይ ባለው መንግሥቱን በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ሙሉ በሙሉ በመካፈል ለአገልግሎቱ ያለን ቅንዓት እንዳይቀዘቅዝ ጠንክረን እንሥራ!