“በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ”
1. የስብከቱን ሥራ ማከናወን ያለብን በምን ዓይነት መንፈስ ነው?
1 በየትኛውም ክርስቲያናዊ የአገልግሎት ዘርፍ የቀዘቀዘ መንፈስ ማሳየት አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ “በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ” እንዲሁም ይሖዋን “እንደ ባሪያ አገልግሉ” የሚል ማበረታቻ ተሰጥቶናል። (ሮም 12:11) ይሁን እንጂ ለአገልግሎቱ ያለን ቅንዓት እንዲቀዘቅዝ የሚያደርጉ በርካታ ነገሮች አሉ። ታዲያ ለመንግሥቱ አገልግሎታችን ያለንን ቅንዓትና ጉጉት ‘እንደ እሳት ማቀጣጠል’ የምንችለው እንዴት ነው?—2 ጢሞ. 1:6, 7
2. የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግ በቅንዓት ከማገልገል ጋር ምን ግንኙነት አለው?
2 የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፦ አንድ ሰው ውጤታማ የመንግሥቱ ሰባኪ እንዲሆን ከተፈለገ የአምላክን ሕግ የሚወድና በቃሉ ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች ከልቡ የሚቀበል መሆን ይኖርበታል። (መዝ. 119:97) የግል ጥናት ስናደርግ የምናገኛቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ልባችን ለሥራ እንዲነሳሳና ቅንዓታችን እንዲቀጣጠል ያደርጋሉ። እነዚህን እውነቶች ለሰጠን አካል ያለን ፍቅርና ምሥራቹን ለሌሎች ለማካፈል ያለን ጉጉት ለአምላክ ውዳሴ እንድናቀርብና ስሙን በይፋ እንድናውጅ ያነሳሳናል። (ዕብ. 13:15) ምሥራቹን በቅንዓት መስበካችን ለመልእክቱ ትልቅ ዋጋ እንደምንሰጥ በግልጽ ያሳያል።
3. የአምላክ መንፈስ በአገልግሎታችን ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?
3 የአምላክን መንፈስ ለማግኘት ጸልዩ፦ በራሳችን ኃይል ውጤታማ አገልግሎት ማከናወን አንችልም። ትክክለኛ ቅንዓት ሊኖረን የሚችለው የአምላክ መንፈስ በውስጣችን በነፃነት ሲሠራ ነው። (1 ጴጥ. 4:11) ‘የታላቅ ኃይል’ ምንጭ ወደሆነው አካል ከቀረብን በድፍረት እንድንሰብክ የሚያስችለንን መንፈሳዊ ብርታት እናገኛለን። (ኢሳ. 40:26, 29-31) ሐዋርያው ጳውሎስ በአገልግሎቱ ፈተና ባጋጠመው ጊዜ ‘ከአምላክ እርዳታ አግኝቷል።’ (ሥራ 26:21, 22) ታላቅ ብርታት የሚሰጠው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ በአገልግሎታችን የጋልን እንድንሆን ስለሚያደርገን ይህን መንፈስ ለማግኘት መጸለይ ይገባናል።—ሉቃስ 11:9-13
4. ቅንዓት ማሳየት የሚያስገኛቸው ግሩም ውጤቶች ምንድን ናቸው? ይሁንና ምን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን?
4 ለመንግሥቱ ስብከት ሥራ የጋለ ቅንዓት ያለን መሆኑ አብዛኛውን ጊዜ የክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ቅንዓት ይበልጥ እንዲቀጣጠል ያደርጋል። (2 ቆሮ. 9:2) በክልላችን ውስጥ ለምናገኛቸው ሰዎች ምሥራቹን በቅንዓትና ጽኑ እምነት እንዳለን በሚያሳይ መንገድ የምንሰብክላቸው ከሆነ መልእክቱን መቀበል ይበልጥ ቀላል ይሆንላቸዋል። ይሁንና ቅንዓት ከማሳየት ባሻገር ምንጊዜም ዘዴኞችና ገሮች መሆን አለብን። (ቲቶ 3:2) ሁልጊዜም ቢሆን የቤቱን ባለቤት በአክብሮት ለመያዝ ብሎም የመምረጥ ነፃነቱን ለማክበር ጥረት እናደርጋለን።
5. የትኛውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በሥራ ለማዋል መጣር ይኖርብናል?
5 የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እንደመሆናችን መጠን ምንጊዜም ‘በመንፈስ የጋልን እንሁን።’ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማድረግና መንፈስ ቅዱስን ሊሰጠን ወደሚችለው ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ቅንዓታችንን እናሳድግ። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ “በመንፈስ ቅዱስ እንዲሁም በጽኑ እምነት” በመስበክ አገልግሎታችንን በቅንዓት ማከናወን እንችላለን።—1 ተሰ. 1:5