ዛሬ ነገ እያልክ ነው?
ምኑን? ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ለተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የሕክምና መመሪያ ካርድ መሙላቱን። ‘ነገ የሚሆነውን ስለማታውቅ’ ድንገተኛ ሁኔታ አጋጥሞህ ሐኪም ቤት ብትገባ ምን ዓይነት ሕክምናዎችን እንደምትፈልግ አስቀድመህ መወሰንህና ይህን ውሳኔህን በጽሑፍ ማስፈርህ እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። (ያዕ. 4:14፤ ሥራ 15:28, 29) በደም ምትክ የሚሰጥ ሕክምና—የሕሙማንን መብትና ፍላጎት ማክበር የተባለው ቪዲዮ የተዘጋጀው በዚህ ረገድ አንተን ለመርዳት ታስቦ ነው። ይህን ቪዲዮ ከተመለከትክ በኋላ ከዚህ በታች በቀረቡት ጥያቄዎች አማካኝነት ትምህርቱን በመከለስ ሁኔታውን በጸሎት አስብበት።—ማሳሰቢያ:- ቪዲዮው ቀዶ ሕክምና ሲደረግ የሚያሳዩ ክፍሎች ስላሉት ወላጆች ከትናንሽ ልጆቻቸው ጋር ፊልሙን ሊያዩት ይገባ እንደሆነና እንዳልሆነ አመዛዝነው መወሰን ይኖርባቸዋል።
(1) በሕክምናው መስክ የተሰማሩ አንዳንድ ሰዎች ደም በመስጠት የሚደረግ ሕክምናን እንደገና ማጤን የጀመሩት ለምንድን ነው? (2) ያለ ደም ከተከናወኑ ከባድ ቀዶ ሕክምናዎች ውስጥ ሦስት ምሳሌዎች ጥቀስ። (3) በዓለም ዙሪያ ሕመምተኞቻቸውን ያለ ደም ለማከም ፈቃደኛ መሆናቸውን የገለጹ ምን ያህል ሐኪሞችና የቀዶ ሕክምና ባለሞያዎች ይገኛሉ? እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኞች የሆኑትስ ለምንድን ነው? (4) በቅርቡ በሆስፒታሎች ውስጥ በተካሄዱ ጥናቶች መሠረት ደም መውሰድን በተመለከተ ምን ነገር ሊታወቅ ችሏል? (5) ደም ከመውሰድ ጋር በተያያዘ ምን ዓይነት የጤና እክሎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ? (6) በርካታ ባለሞያዎች በደም ምትክ የሚሰጡ የሕክምና አማራጮች የሚያስገኟቸውን ጥቅሞች በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል? (7) ደም ማነስ ከምን ይመጣል? ሰዎች ለአደጋ ሳይጋለጡ የደማቸው መጠን ምን ያህል ዝቅ ሊል ይችላል? ሁኔታውን ለማስተካከል ምን ማድረግ ይቻላል? (8) የአንድ ሕመምተኛ ሰውነት ተጨማሪ ቀይ የደም ሕዋስ እንዲያመርት ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? (9) ሐኪሞች በቀዶ ሕክምና ወቅት የሚፈስሰውን ደም ለመቀነስ በየትኞቹ መንገዶች ይጠቀማሉ? (10) በደም ምትክ የሚሰጡ ሕክምናዎች ለትናንሽ ልጆች ወይም ለሕይወት የሚያሰጋ ድንገተኛ አደጋ ላጋጠማቸው ሰዎች ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ? (11) ከጥሩ ሕክምና ተቀዳሚ የሥነ ምግባር መመሪያዎች አንዱ ምንድን ነው? (12) ክርስቲያኖች በደም ምትክ ከሚሰጡ የሕክምና አማራጮች ውስጥ የሚቀበሉትን አስቀድመው መወሰናቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህንን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?
በፊልሙ ላይ የቀረቡ አንዳንድ የሕክምና አማራጮችን መቀበል እያንዳንዱ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነ ሕሊናው ተጠቅሞ የሚያደርገው የግል ውሳኔ ነው። እናንተም ሆናችሁ ልጆቻችሁ ምን ዓይነት ሕክምና እንደምትፈልጉ አስቀድማችሁ ወስናችኋል? በዚህ ጉዳይ ላይ ይበልጥ የተሟላ መረጃ ለማግኘት በሰኔ 15, 2004 እና በጥቅምት 15, 2000 የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ የወጡትን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” እንዲሁም “የደም ክፍልፋዮችንና የራሴን ደም በመጠቀም የሚሰጡ ሕክምናዎችን በተመለከተ ምን ውሳኔ ማድረግ ይኖርብኛል?” የሚለውን በኅዳር 2006 የመንግሥት አገልግሎታችን እትም ላይ የወጣውን አባሪ ተመልከት። የአደጋ ጊዜ ተጠሪዎች እንዲሆኑ የመረጥካቸው ሰዎችና የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ የቤተሰብህ አባላት ያደረግከውን ውሳኔ በሚገባ እንዲያውቁት ማድረግ ይኖርብሃል።