በአገልግሎት ላይ ስትሆኑ እርስ በርሳችሁ ተናነጹ
1 ሁላችንም፣ ሰዎች ‘በወቅቱ በተነገረ ቃል’ አማካኝነት ሲያበረታቱን ደስ ይለናል። (ምሳሌ 25:11 የ1980 ትርጉም) ከሌሎች ጋር በመስክ አገልግሎት አብረን ስንሠራ ጭውውታችን የሚያንጽ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
2 የሚያንጽ ጭውውት:- በስብከቱ ሥራ ስንሰማራ መንፈሳዊ የሆኑ ጉዳዮችንም አንስተን መጨዋወታችን ምንኛ የሚያንጽ ነው! (መዝ. 37:30) ስለ መግቢያዎቻችን አሊያም በቅርቡ በመስክ አገልግሎት ስላገኘነው አስደሳች ተሞክሮ ማውራት እንችላለን። (ሥራ 15:3) ከግል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን ወይም በቅርብ ከደረሱን መጽሔቶች አሊያም ደግሞ ከጉባኤ ስብሰባ አስደሳች ነጥብ አግኝተናል? ከሆነ፣ ያንን ማንሳት እንችላለን። በቅርቡ በጉባኤያችን ቀርቦ ከነበረ የሕዝብ ንግግር ላይ የሰማናቸውን ነጥቦች አንስተን መወያየትም እንችል ይሆናል።
3 የምናነጋግረው ሰው ላነሳው የተቃውሞ ሐሳብ መልስ መስጠት ብንቸገር የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሊሰማን ይችላል። ወደሚቀጥለው ቤት ከመሄዳችን በፊት ጥቂት ደቂቃዎችን በመውሰድ ወደፊት እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን እንዴት መፍታት እንደምንችል ከአገልግሎት ጓደኛችን ጋር መወያየታችን በጣም ጠቃሚ ነው፤ በዚህ ወቅት ምናልባትም ማመራመር የተባለውን መጽሐፍ መጠቀም እንችል ይሆናል። የአገልግሎት ጓደኛችን ጥሩ አቀራረብ እንደተጠቀመ ካስተዋልን ልባዊ የሆነ የአድናቆት ቃል በመናገር ልናበረታታው እንችላለን።
4 ቅድሚያውን ውሰዱ:- ከመጽሐፍ ጥናት ቡድናችን ውስጥ በቅርቡ አብረናቸው ያላገለገልን አንዳንድ አስፋፊዎች ይኖሩ ይሆን? አብረውን እንዲያገለግሉ መጋበዛችን ‘እርስ በርሳችን ለመበረታታት’ የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍትልናል። (ሮሜ 1:12) የዘወትርና ረዳት አቅኚዎች፣ አገልግሎት የሚወጡ አስፋፊዎች ጥቂት በሚሆኑበት ጊዜ በተለይ ደግሞ ማለዳ ወይም አመሻሹ ላይ አብረዋቸው የሚያገለግሉ አስፋፊዎችን ማግኘታቸው ያስደስታቸዋል። አብረናቸው ለማገልገል ራሳችንን በማቅረብ አቅኚዎችን መደገፍ እንችላለን። እንደ ልብ ለማገልገል የሚያስችል ጥሩ ጤንነት የሌለው አስፋፊ ይኖር ይሆን? እንደነዚህ ያሉ አስፋፊዎች ምናልባትም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምናስጠናበት ጊዜ አብረውን እንዲሆኑ ዝግጅት ማድረጉ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።—ምሳሌ 27:17
5 በጥቃቅን ጉዳዮችም ጭምር ማመስገንና አድናቆትን መግለጽ ምንጊዜም ያበረታታል። እንግዲያው በመስክ አገልግሎት ከሌሎች ጋር አብረን ስንሠራ ይህንን በአእምሯችን ልንይዝ ይገባል፤ እንዲህ ማድረጋችን ሁልጊዜ ‘እርስ በርስ መተናነጽ’ እንደምንፈልግ ያሳያል።—1 ተሰ. 5:11