ከቤት ወደ ቤት ስታገለግሉ ጥሩ ረዳት ሁኑ
1. በአገልግሎት ላይ ከሌላ ሰው ጋር አብሮ መሥራት ምን ጥቅሞች አሉት?
1 በአንድ ወቅት ኢየሱስ 70 ደቀ መዛሙርትን እንዲሰብኩ ልኳቸው ነበር፤ በዚህ ጊዜ “ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው።” (ሉቃስ 10:1) ይህ ዝግጅት ደቀ መዛሙርቱ በሚሰብኩበት ጊዜ እርስ በርስ መረዳዳትና መበረታታት እንዳስቻላቸው ምንም ጥርጥር የለውም። እኛስ ከሌላ አስፋፊ ጋር አብረን ስናገለግል እርዳታ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው?
2. የአገልግሎት ጓደኛችን ሰዎችን በሚያናግርበት ጊዜ ማዳመጥ የሚኖርብን እንዴት ነው? ለምንስ?
2 በማዳመጥ፦ የአገልግሎት ጓደኛህ ሰዎችን ሲያነጋግር በጥሞና አዳምጥ። (ያዕ. 1:19) ጥቅስ የሚነበብ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስህን አውጥተህ ተከታተል። እየተናገረ ያለው የአገልግሎት ጓደኛህም ይሁን የቤቱ ባለቤት ዓይንህ ምንጊዜም ተናጋሪው ላይ ይሁን። ውይይቱን በትኩረት መከታተልህ የቤቱ ባለቤት ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርግ ሊያነሳሳው ይችላል።
3. የአገልግሎት ጓደኛችን እንድንናገር የሚጋብዘን መቼ ሊሆን ይችላል?
3 መቼ መናገር እንዳለብን አስተዋይ በመሆን፦ የአገልግሎት ጓደኛችን አንድን ሰው በሚያናግርበት ጊዜ እሱ ራሱ ቀዳሚ ሆኖ ውይይቱን እንዲያደርግ በመተው እንደምናከብረው ማሳየት እንችላለን። (ሮም 12:10) በውይይቱ መሃል ጣልቃ መግባት አይኖርብንም። አብረነው የምናገለግለው ሰው መናገር የፈለገው ነገር ከጠፋበት አሊያም የቤቱ ባለቤት ተቃውሞ ወይም ጥያቄ ካነሳና ጓደኛችን እንድንረዳው ከጠየቀን ሌላ ርዕሰ ጉዳይ ከማንሳት በመቆጠብ እሱ በተናገረው ሐሳብ ላይ ተመርኩዘን ተጨማሪ ነጥብ ለመጥቀስ ጥረት ማድረግ አለብን። (ምሳሌ 16:23፤ መክ. 3:1, 7) መናገር ካለብን የምንናገረው ነገር እየተሰጠ ላለው ምሥክርነት ድጋፍ የሚሰጥ መሆን አለበት።—1 ቆሮ. 14:8
4. በአገልግሎት ለምናገኘው ደስታና ስኬት አስተዋጽኦ የሚያደርገው ምንድን ነው?
4 ሠላሳ አምስቱ ጥንድ ደቀ መዛሙርት ስብከታቸውን ሲጨርሱ ‘ደስ እያላቸው ተመልሰዋል።’ (ሉቃስ 10:17) ከቤት ወደ ቤት አብረናቸው የምናገለግላቸውን ሰዎች ስንረዳ የምናዳምጥ እንዲሁም መቼ መናገር እንዳለብን የምናስተውል ከሆነ እኛም በአገልግሎታችን ደስተኛና ስኬታማ መሆን እንችላለን።