በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙትን ሰዎች እንዴት መርዳት እንችላለን?
1. መጋቢት 22, 2008 ላይ ምን ከፍተኛ ምሥክርነት ይሰጣል?
1 መጋቢት 22, 2008 ላይ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከፍተኛ ምሥክርነት ይሰጣል። በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙ ሰዎች፣ ይሖዋ ለሰው ልጆች ቤዛውን በመስጠት ስላሳየው ታላቅ ፍቅር ትምህርት ሲሰጥ ያዳምጣሉ። (ዮሐ. 3:16) ከዚህም በተጨማሪ ስለ መንግሥቱና ይሖዋ ይህን መንግሥት በመላው ምድር ላይ ፈቃዱን ለማስፈጸም እንዴት እንደሚጠቀምበት ይማራሉ። (ማቴ. 6:9, 10) የአምላክ ሕዝቦች ያላቸውን ፍቅርና አንድነት በገዛ ዓይናቸው የሚያዩ ሲሆን ሞቅ ያለው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈሳችንንም ያጣጥማሉ።—መዝ. 133:1
2. በበዓሉ ላይ የሚገኙትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
2 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች:- በበዓሉ ላይ ከሚገኙት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በቅርቡ መጽሐፍ ቅዱስን ከእኛ ጋር ማጥናት የጀመሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ጥናቶችህን ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር አስተዋውቃቸው። በሳምንት ውስጥ ስለምናደርጋቸው ስብሰባዎች ግለጽላቸው፤ እንዲሁም የመንግሥት አዳራሹን አስጎብኛቸው። የመታሰቢያውን በዓል ንግግር የሚያቀርበው ወንድም ንግግሩን በሚሰጥበት ወቅት እንዲህ ያሉ ጥናቶች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ያበረታታቸዋል። አንተም ተናጋሪው የሚሰጣቸውን ሐሳቦች ተጠቅመህ ጥናቶችህን ማበረታታት ትችላለህ።
3. በበዓሉ ላይ የተገኙትን የቀዘቀዙ አስፋፊዎች ለማበረታታት ምን ማድረግ ይቻላል?
3 የቀዘቀዙ አስፋፊዎች:- ወደ በዓሉ ከሚመጡት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ የቀዘቀዙ አስፋፊዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ቅድሚያውን በመውሰድ ሞቅ ያለ ሰላምታ እንስጣቸው። ስለ ግል ጉዳዮቻቸው አላስፈላጊ ጥያቄዎችን ከመጠየቅ ወይም ሊያሸማቅቋቸው የሚችሉ ቃላቶችን ከመናገር እንቆጠብ። የመታሰቢያው በዓል ከተከበረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሽማግሌዎች በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ የቀዘቀዙ አስፋፊዎችን ቀርበው ማነጋገር ይገባቸዋል። በዚህ ወቅት በበዓሉ ላይ ለመገኘት ስላደረጉት ጥረት ማመስገንና በሚቀጥለው የጉባኤ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ሞቅ ያለ ግብዣ ማቅረብ ይችላሉ።
4. እያንዳንዳችን ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶችን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
4 እንግዶች:- በበዓሉ ላይ ለመገኘት ከሚመጡት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በግል የጋበዝናቸው የምናውቃቸው ሰዎች አሊያም የቤተሰባችን አባላት ሊሆኑ ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ በበዓሉ ላይ የሚገኙት በልዩ ዘመቻው ወቅት የመጋበዣ ወረቀት ደርሷቸው ይሆናል። አዳዲስ ሰዎችን ካየህ ቅድሚያውን ወስደህ ተዋወቃቸው፤ እንዲሁም በመምጣታቸው መደሰትህን ግለጽላቸው። እነዚህ እንግዶች ከዚህ በፊት በስብሰባዎቻችን ላይ ተገኝተው የማያውቁ ይሆናሉ። በጭውውታችሁ መሃል በሌላ ጊዜ መገናኘት የምትችሉበትን መንገድ ታገኝ ይሆናል። የመታሰቢያው በዓል ከተከበረ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሄደህ በመጠየቅ አሊያም ስልክ በመደወል ፍላጎታቸውን ለማሳደግ መጣር እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ ግብዣ ማቅረብ ትችላለህ።
5. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ምን ማለት እንችላለን?
5 በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ለማስተዋወቅ በመታሰቢያው በዓል ንግግር ላይ የቀረቡትን ሐሳቦች መጠቀም ይቻላል። ለምሳሌ ያህል፣ የመታሰቢያውን በዓል ንግግር የሚያቀርበው ወንድም ኢሳይያስ 65:21-23ን ያነብ ይሆናል። በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት ንግግሩን በማስታወስ “ቤዛው የሚያስገኛቸው ሌሎች በረከቶች ምን እንደሆኑ ባሳይዎ ደስ ይለኛል” ማለት ይቻላል። ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከተባለው መጽሐፍ ገጽ 4-5 ላይ ያሉትን ሐሳቦች አሳየው። አሊያም ደግሞ እንዲህ ማለት ይቻላል:- “‘ብዙዎች የኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼ ነው?’ ብለው ይጠይቃሉ።” ከዚያም በምዕራፍ 9 ላይ የሚገኙትን የመጀመሪያዎቹን 3 አንቀጾች ተወያዩባቸው። ጥናት ለማስጀመር የሚረዳን ሌላው አማራጭ ደግሞ የመታሰቢያውን በዓል ንግግር የሚያቀርበው ወንድም የሰጣቸውን ሐሳቦች ከጠቀስን በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ በማስተዋወቅ እንዴት እንደሚጠና ማሳየት ነው።
6. ኢየሱስ በሰጠን ትእዛዝ መሠረት በሞቱ መታሰቢያ በዓል ላይ ስንገኝ ምን አጋጣሚዎች ይከፈቱልናል?
6 እያንዳንዳችን በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን፣ የቀዘቀዙ አስፋፊዎችን እንዲሁም እንግዶችን ለመርዳት የምናገኘውን አጋጣሚ ለመጠቀም ንቁዎች እንሁን። (ሉቃስ 22:19) ይሖዋ፣ የመንግሥቱን አገልግሎት ከፍ ለማድረግ የምናደርገውን ማንኛውንም ጥረት እንደሚባርክ ምንም አያጠራጥርም።