ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ የምንጋብዝበት ልዩ ቀን
1 ከጥር ወር አንስቶ እያንዳንዱ ጉባኤ፣ አስፋፊዎች ልዩ ትኩረት ሰጥተው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ጥረት እንዲያደርጉ በየወሩ አንድ ቅዳሜ ወይም እሁድ ይመድባል። ይህ ቀን በወር ውስጥ ካሉት ሳምንታት በአንዱ ምናልባትም በመጀመሪያው ሳምንት ላይ ሊውል ይችላል። እንደ ክልሉ ሁኔታ አንዳንድ ጉባኤዎች ቅዳሜን ሌሎች ደግሞ እሁድን ሊመርጡ ይችላሉ። በዚህ ቀን አስፋፊዎች ሲያገለግሉ፣ የቤቱ ባለቤት መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፈቃደኛ ባይሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ወይም አዳዲስ መጽሔቶችን ማበርከት ይችላሉ። ሁሉም ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች፣ በዚህ የአገልግሎት እንቅስቃሴ ለመካፈልና አስፋፊዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር እንዲችሉ ለመርዳት የተቻላቸውን ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።
2 የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ ይህ ልዩ ቀን በየትኛው ሳምንት ላይ ቢውል የተሻለ እንደሚሆን ይወስናል። አስፋፊዎች ከቤት ወደ ቤት በሚያገለግሉበትና ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ተመልሰው ሄደው በሚያነጋግሩበት ጊዜ አስቀድመው ጥሩ ዝግጅት በማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ልዩ ጥረት እንዲያደርጉ አልፎ አልፎ ማሳሰቢያ መስጠት አስፈላጊ ነው።
3 ዝግጅት ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚረዱ ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችን በጥር 2006 የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ ላይ እንዲሁም ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ገጽ 12 ላይ ማግኘት እንችላለን። አንዳንዶች ደግሞ እውነቱን ማወቅ ትፈልጋለህ? የሚለውን ትራክት መጠቀም ይመርጡ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ በነሐሴ 2007 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 6 ላይ የወጣው ርዕስ፣ መጽሔት ያበረከትንላቸውን ሰዎች ተመልሰን ሄደን በምናነጋግርበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር የምንችልባቸውን መንገዶች ይጠቁማል። ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ከ10 እስከ 15 ደቂቃ የሚቆይ አጭር የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ እንዲመሩ ይመደባሉ፤ በዚህ የስምሪት ስብሰባ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚረዱ ጥቂት ጠቃሚ ሐሳቦች ሊብራሩ አሊያም በሠርቶ ማሳያ መልክ ሊቀርቡ ይገባል።
4 እርግጥ ነው፣ የምናነጋግረው ሰው ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይጀምራል ወይም ጥናቱን ይገፋበታል ብለን መጠበቅ አንችልም። ይህ ግን ሰዎችን ጥናት ለማስጀመር ጥረት ከማድረግ ወደኋላ እንድንል ሊያደርገን አይገባም፤ ምክንያቱም በግ መሰል ሰዎችን ወደ ድርጅቱ የሚስበው ይሖዋ ነው። (ዮሐ. 6:44) የተጣለብን ኃላፊነት የእውነትን ዘር መዝራት ብቻ ሳይሆን ውኃ ማጠጣትና መንከባከብ ይጠይቃል፤ ይህ ደግሞ ቅን ልብ ካላቸው ሰዎች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትን ይጨምራል። እንዲህ በማድረግ ከአምላክ ጋር ተባብረን እንደምንሠራ በተግባር እናሳያለን።—1 ቆሮ. 3:9