የጥያቄ ሣጥን
◼ መስበካችሁን እንድታቆሙ ብትታዘዙ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል?
አስፋፊዎች በአንድ ዓይነት የአገልግሎት መስክ እየተካፈሉ ሳለ ፖሊሶች መጥተው አስፋፊዎቹ ሕግ እንደጣሱ በመግለጽ መስበካቸውን እንዲያቆሙ የሚያዙበት ጊዜ አለ። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠማችሁ አክብሮት በተሞላበት መንገድ ወዲያውኑ ክልሉን ለቃችሁ መውጣት ይኖርባችኋል። (ማቴ. 5:41፤ ፊልጵ. 4:5) ሕጋዊ መብት እንዳለን በመግለጽ ችግሩን በራሳችሁ ለመፍታት አትሞክሩ። የሚቻል ከሆነ የፖሊሱን መለያ ቁጥርና የተሠማራበትን አካባቢ (ወይም ቁጥሩን) በዘዴ ለመያዝ ጥረት አድርጉ። ከዚያም ወዲያውኑ ሁኔታውን ለሽማግሌዎች አሳውቁ፤ እነሱ የተፈጠረውን ሁኔታ ለቅርንጫፍ ቢሮው ሪፖርት ያደርጋሉ። በተመሳሳይም በአፓርታማ ውስጥ እያገለገላችሁ እያለ የጥበቃ ሠራተኞች ወይም ሌላ ማንኛውም የአፓርታማው ተወካይ ሕንፃውን ለቅቃችሁ እንድትወጡ ቢጠይቋችሁ ወዲያውኑ የተባላችሁትን ማድረግ ይኖርባችኋል፤ ከዚያ በኋላ ግን ሁኔታውን ለሽማግሌዎች አሳውቁ። ሥልጣን ያላቸውን ሰዎች በገርነትና በትሕትና መንፈስ መያዛችን አላስፈላጊ ችግር እንዳይፈጠር ሊረዳ ይችላል።—ምሳሌ 15:1፤ ሮም 12:18